ህብረተሰቡ በሃዋሳ በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

72
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2010 በሲዳማ የዘመን መለወጫ ጫምባላላ በአል ላይና ከዚያ በኋላ በነበረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባችው የወላይታ ተወላጆች ህብረተሰቡ እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ። የአዲስ አበባ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ጋር ጉዳት ለደረሰባቸው አፋጣኝ እርዳታ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ መክሯል። የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጉዳት የደረሰባቸውና በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች በቂ ምግብ እያገኙ አይደለም። በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በገንዘብ፣ በምግብና ቁሳቁሰ የአቅሙን እርዳታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ገንዘብ መርዳት የሚፈልግ ወገን የወላይታ ልማት ማህበር በከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 100064442604 ገቢ ማድረግ እንደሚችል ተገልጿል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግዛው ዮሃንስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በክልል የመኖርና ሃብት የማፍራት ህገ -መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ መኖር እንደሚችል ይገልጻሉ። በመሆኑን ጉዳቱ እንዲደርስ ያደረጉ በህግ እንዲጠየቁ በሚደረገው ሂደት እስከመጨረሻው ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በተመቻቸው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ከ300 በላይ የሚሆኑ የወላይታ ተወላጆች የተገኙ ሲሆን ከተሳታፊዎች የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ተካሂዷል። በቀጣይ ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ሊከናወኑ እንደሚችሉም ከኮሚቴው ሰምተናል። የሲዳማ ዘመን መለወጫ በሆነው የጫምባላላ በአል የተከሰተው ግጭት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስፍራው አቅንተው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም