ሚኒስቴሩ በህዝቡ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችን ለመግታት የሚሞክሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀ

83
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2010 በህዝቡ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችን ለማጥቃት የሚሞክሩ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች የህዝብን ሰላም ከማደፍረስ እንዲቆጠቡ  መከላከያ ሚኒስቴር አስጠነቀቀ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በህዝቡ ውስጥ እየፈነጠቀ ያለውን ብሩህ ተስፋ ምክንያት በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ምስጋናና ድጋፍ ለመግለጽ በወጣው ዜጋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዟል። ሚኒስቴሩ በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የህዝቡንና የአገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን ከመንግስትና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመመከት ሁሌም ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል። ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲሁም በህዝቡ እየተመዘገቡ ያሉትን ድሎች በኃይል ለመቀልበስ የሚሞከሩ ማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች የህዝብን ሰላም ከማደፍረስ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲልም አሳስቧል። በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደባባይ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ በተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰላማዊ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም