ለስፖርት ውርርድ(ቤቲንግ) የሚሰጠው ፈቃድ ለጊዜው ታገደ

86
ኢዜአ፤ጥር/2012 ለስፖርት ውርርድ(ቤቲንግ) የሚሰጠው ፈቃድ በጊዜያዊነት መታገዱን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ። አስተዳደሩ በስፖርት ውርርድ ፈቃድ አግኝተው በሚሰሩ ቤቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥርም እንደሚያጠናክር አስታውቋል። የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ ላለፉት ሁለት ወራት በስፖርት ውርርድ ላይ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። በጥናቱ ላይ ከስፖርት ውርርድ ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉንና የተለያዩ ክፍተቶች እንደተለዩም ተናግረዋል። በጥናቱ መሰረት በስፖርት ውርርድ ቤቶች ውስጥ ተገቢ የሆነ የወጪና ገቢ የሂሳብ አያያዝ የሰነድ ስርአት አለመኖሩ እንደ ችግር የሚታይ ነው ብለዋል። ያለ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እውቅና ውጭም ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱም ገልጸዋል። የስፖርት ውርርድ ፈቃድ (ቤቲንግ) በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ 135/1999 በመመሪያ 83/2005 መሠረት የሚሰጥ ነው። በመመሪያውም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ውርርዱን ማድረግ እንደማይችሉ ያስቀምጣል። ነገር ግን የስፖርት ውርርድ ቤቶች ከ18 ዓመት በታች የሆናቸውን ታዳጊዎች በውርርድ ውስጥ እንደሚያሳተፉም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያመለከቱት። አቶ ቴዎድሮስ አክለውም በ2005 ዓ.ም የወጣው መመሪያ አሁን ወቅቱ ከደረሰበት ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ማሻሻያ የሚያስፈልገው ሆኖ ተገኝቷልም ብለዋል። በተጨማሪም የስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ ያለው የቁጥጥር ስርአትም ጠንካራ እንዳልሆነም አንስተዋል። በዚሁ መሰረት ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱና ቁጥጥሩን ይበልጥ ለማጠናከር ለስፖርት ውርርድ(ቤቲንግ) የሚሰጠው ፈቃድ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ተደርጓል ብለዋል። የስፖርት ውርርዱ በኢትዮጵያ ሲጀመር ብዙ ሰዎች የሚጫወቱበት እንዳልነበረና አሁን በውርርዱ ላይ የሚሳተፋ ዜጎች እየጨመረ መምጣቱ ቁጥጥሩን ማጠናከር እንደሚያሻም አቅጣጫ የተቀመጠበት ጉዳይ እንደሆነም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት። አስተዳደሩ ቁጥጥርን የሚያደረግ ግብረ ሃይል አቋቁሞ በዚህ ሳምንት ወደ ስራ እንደሚገባም አመልክተዋል። በስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ ምን አይነት ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል?  ሲል ኢዜአ ጥያቄውን አንስቷል። "ፈቃድ ማገድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፤ በግብረ ሃይሉ በሚደረገው የቁጥጥር ስራ ደግሞ ሌሎች እርምጃዎች ይወሰዳሉ" ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ምላሽ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሚሰጥ ፈቃድ በጊዜያዊነት አገደ እንጂ ቀድመው ፈቃድ የወሰዱ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ስራቸውን መቀጠል እንደሚችሉም አመልክተዋል። የስፖርት ውርርድ(ቤቲንግ) የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እየፈጠረ ነው የሚባለው ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነና ያለ ጥናት ቀውስ አድርሷል ብሎ መደምደም ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል። እስካሁን በዘርፉ ለ43 የስፖርት ውርርድ ቤቶች ፈቃድ መሰጠቱንና ከነዚህም ውስጥ 30ዎቹ በስራ ላይ 13ቱ ወደ ስራው ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ እንደሆኑ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም