ህዝቡ በመስቀል አደባባይ በተፈጠረው ድርጊት ሳይደናገጥ የተጀመረውን የዴሞክራሲና ፍትህ ለውጥ እንዲደግፍ ተጠየቀ

73
አዲስ አበባ ሰኔ17/2010 ህዝቡ ትናንት በመስቀል አደባባይ በተፈጠረው ድርጊት ሳይደናገጥ የተጀመረውን የዴሞክራሲና ፍትህ ለውጥ እንዲያበረታታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለማመስገን የተዘጋጀው ሰልፍ አስተበባሪ ኮሚቴ አሳሰበ። ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ ህዝቡ በጥቃቱ ለተጎዱት ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል። ''ለውጥን እንደገፍ ዲሞክራሲን እናበርታ'' በሚል መሪ ሀሳብ መስቀል አደባባይ የተደረገው ሰልፍ የፍቅር፣ የሰላም፣ የምስጋናና ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድ ላይ የመደመር ቃላቸውን የገለፁበትና ቃል የገቡበት እንደሆነ ተነግሯል። የድጋፍ ሰልፉ አስተባበሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጉደታ ገላልቻ በሰልፉ መጨረሻ አካባቢ የተፈጠረው የቦንብ ፍንዳታ የሁሉንም ልብ የሰበረ መሆኑን ገልፀዋል። በፍንዳታው ህይወታቸውን ላጡት መፅናናትን ተመኝተው ሆስፒታል ለሚገኙት የደም እጥረት በመከሰቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደም በመለገስ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ህዝቡ በተከሰተው ድርጊት ሳይደናገጥ የተጀመረውን የዲሞክራሲና ፍትህ መሻሻል እንዲያበረታታ ጠይቀዋል የኮሚቴው አባል አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸው ህዝቡ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ደህንነቱን በመጠበቁና ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥ በኩል ለሰራው ስራ ምስጋና አቅርበዋል። ዝግጅቱ ከመደረጉ በፊት ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ሰልፉ በሚደረግበት አካባቢ ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይኖር የጠየቁ ቢሆንም ባቡር ሲመላለስ እንደነበር ገልፀዋል። ከመድረኩ ጀርባ ከሰልፉ ጋር የማይገናኝ ሙዚቃ በተደጋገሚ ሲረብሻቸው እንደነበርም ተናግረዋል። ትናንት በደረሰው ጥቃት ሁለት ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈና ከ150 በላይ የሚሆኑት ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል። በሰልፉ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የተሳተፈበት እንደሆነ ይገመታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም