በብድር አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምክንያት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም...በትግራይ የመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች

87
ማይጨው ሰኔ17/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን የመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በብድር አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምክንያት ተጠቃሚ መሆን ባለመቻላቸው ቅሬታቸውን ገለጹ። በአካባቢያቸው ያለውን የብድር አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ እንዲሻሻል ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብበትም እስካሁን ድረስ መሻሻል አልታየም ሲሉም አንቀሳቃሾቹ ተናግረዋል። በዞኑ የሚገኙ የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በስራ እንቅስቃሴያቸውና ባሉባቸው ችግሮች ላይ የሚመክርና ከስምንት ወረዳዎች የተውጣጡ ከ400 በላይ አንቀሳቃሾች የተሳተፉበት መድረክ በአላማጣ ከተማ ተካሄዷል። ከአንቀሳቃሾች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሐጉስ ፍሳሃ በደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም የሚሰጠው የብድር አቅርቦት አነስተኛ ከመሆኑ ባለፈ ገንዘቡን በወቅቱ ለማግኘት ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑን ተናግረዋል። በእዚህም ወደ ተሻለ የንግድ ሥራ ለመሸጋገር መቸገራቸውን ነው የገለጹት። " በተቋሙ ውስጥ በቁጠባ መልክ ያስቀመጡት ገንዘብም ከአላማጣ ከተማ ውጪ ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች ስንቀሳቀስ አውጥቼ መጠቀም የምችልበት አሰራር ባለመኖሩ በስራዬ ላይ  ችግር እየፈጠረብኝ ነው " ብለዋል። የብረት ውጤቶች ድርጅት ለመክፈት የአንድ ሚሊዮን ብር ብድር ለደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም ማቅረባቸውን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ የመኾኒ ከተማ ነዋሪ አቶ አብርሃ ገብረኢየሱስ ናቸው። በተያዘው ዓመት መስከረም ወር ላይ ያቀረቡት የብድር ጥያቄ ከአራት ወር እንግልትና ድካም በኃላ ምላሽ ቢያገኙም ይሰጥሀል የተባሉት የገንዘብ መጠን ባለማግኘታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። የብድር ሰጪው ተቋም ቅርንጫፍ 500 ሺህ ብር ብድር እንደሚፈቀድላቸው ቢያሳውቃቸውም የብድር ሰጪው ተቋም ዋና መስሪያ ቤት ውሉን በማፍረስ 200 ሺህ ብር ብቻ እንደሰጣቸው ገልጸዋል። "አሰራሩ ግልፅ ባይሆንም በከተማው ያሉ ሌሎች ግለሰቦች ለጠየቁት የ500 ሺህ ብር ብድር ሳይጉላሉ እያገኙ ናቸው" ያሉት አቶ ሐጎስ፣ ይህም በተቋሙ ውስጥ የአሰራር ግልጽነት አለመኖሩን እንደሚያሳይ አመልክተዋል። በዞኑ የመኾኒ ከተማ ነዋሪ አቶ በርሄ ረታ በበኩላቸው፣ በተቋሙ የሚሰጠው የብድር ጣሪያ አነስተኛ ከመሆን ባለፈ የተፈቀደውን አነስተኛ የብድር ገንዘብም ተቆራርጦ  የሚሰጣቸው በመሆኑ የጀመሩትን  የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ድርጅታቸውን የማቋቋም እቅዳቸውን ለማሳካት እንደተቸገሩ ተናግረዋል። "መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለማግኘት ያለባቸውን ውስብስብ ችግሮች እየታወቀ ይህን ወደ ጎን በማለት አሁንም ብድር እንደተሰጣቸው ተደርጎ  የሚቀርብ  ሪፖርት መታረም ይገባዋል" ብለዋል። በውይይቱ ማብቂያ  ላይ የተገኙት የዞኑ  ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ  ኃላፊ አቶ አስመላሽ ረዳ እንዳሉት፣  መምሪያው ለኢንተርፕራይዞች ብድርና ስልጠና ማመቻቸት ዋነኛ ተግባሩ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ችግሮቻቸው የሚፈታው በመታገል በመሆኑ አገልግሎትን በጥቅም በማዛበት ችግር የሚፈጥሩ ተቋማት ካሉ በማጋለጥ ከመንግስት ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። በጉዳዩ ላይ ምላሽ የተጡት የትግራይ ደቡባዊ ዞን የደደቢት ብድርና ቁጠባ አክሲዮ ማህበር  ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ተስፋይ ገብረጊዎርጊስ  ተቋሙ ለሞዴል ኢንተርፕራይዞች እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ብድር እንደሚሰጥ አመልክተዋል። ኢንተርፕራይዞቹ  የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት የመኖሪያ ቤት የባለቤትነት ካርታና ደረጃውን የጠበቀ የንግድ ሥራ ዕቅድ ሲያቀርቡ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና በአካባቢው የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች  የራሳቸውን  የንግድ ሥራ ዕቅድ ማዘጋጀት ሲገባቸው የሌሎችን ኮርጀው ስለሚያቅርቡ የብድር ጥያቄያቸው ውድቅ እንደሚሆንባቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም