በኦሮሚያ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረትና ተሳትፎ ሊደርግ እንደሚገባ ተመለከተ

69
ኢዜአ ጥር 3/2012 በኦሮሚያ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ሁሉም አካል የተቀናጀ ጥረትና ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተመለከተ። የክልሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን  ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የትራንስፖርት ቀንን በማስመልከት አረአያ ለሆኑ ሹፌሮች ዛሬ በአዳማ ከተማ እውቅና ሰጥቷል። በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ አህመድ አባጊሳ እንዳሉት በክልሉ የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ እየጨመረ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፈው ዓመት ብቻ በክልሉ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአንድ ሺህ 824 ሰዎችን ሕይወት ማለፉን አስታውሰው "ዘንድሮም አደጋው ተባብሶ ቀጥሏል "ብለዋል። የአደጋውን መንስኤ በማስመልክት ባለስልጣኑ ሰፊ ጥናት ማካሄዱን ጠቅሰው በተለይ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብልሽት፣የጥንቃቄ ጉድለት፣የትራፊክ ህግና ደንብ አለማክበር ለአደጋው በመንስኤነት ተጠቅሰዋል። እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ሁሉም አካል የተቀናጀ ጥረትና ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተው በተለይ ተሳፋሪዎች ትርፍ ሰው ሲጫን በመቃወም ለትራፊክ ህግና ደንብ መከበር ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ ባለስልጣኑ በተያዘው ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የተጠያቂነትን አሰራር ለማጠናከር አቅዶ እየሰራ ነው።። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ታምራት ዳባ በበኩላቸው በክልሉ ችግሩን ለመከላከል በስነ ምግባር የታነጹ አሽከርካሪዎች ለማፍራትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ  ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ በግማሽ የበጀት ዓመቱ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ837 ሰዎችን ህይወት ማለፉን ያስታወቁ ደግሞ  የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራፊክ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ተመስገን ናቸው። "የደረሰው የህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጨምሮ ታይቷል "ያሉት ዳይሬክተሩ አደጋውን ለመቀነስ በቀጣይ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ባለስልጣኑ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል የቁጥጥር ስራው በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ የራዳር ግዥ  በመፈጸም ለየዞኖቹ ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ፍጥነት የሚገድብ አሰራር እውን ለማድረግ የሙከራ አሰራር ተግባራዊ እየሆነ ነው። የትራንስፖርት ቀንን በማስመልከት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ለጅም ዓመታት በማሽከርከር አደጋ ያላደረሱና ምስጉን ለሆኑ 80 ሹፌሮች ባለስልጣኑ እውቅና ሰጥቷቸዋል። እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ከሀረር የመጡት አቶ አጀባ ጣሂር በሰጡት አስተያየት ላለፉት 15 ዓመታት ለተሳፋሪ ክብር በመስጠትና ረጋ ብለው በማሽከርከር እንዲሁም የትራፊክ ህግ በማክበራቸው ከአደጋ መጠበቅ እንደቻሉ ተናግረዋል። ከልክ በላይ  ማሽከርከር በዋናነት ለአደጋ ስለሚያጋልጥ አሽከርካሪዎች ለህይወታቸው ቅድሚያ በመስጠት ረጋ ብለው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም አመልክተዋል። " የማሽከረክረውን መኪና ደህንነት ዘውትር በመቆጣጠርና ከሱስ ነፃ በመሆን ሙሉ ትኩረቴን ስራዬ ላይ በማድረግ በማሽከርከሬ ምንም ዓይነት አደጋ አለደረሰብኝ " ያሉት ደግሞ  ሌላው ከባሌ ሮቤ የመጡት የከባድ ተሽከርካሪ ሹፌር ሽፈራው ሃይሉ ናቸው። የትራንስፖርት ቀንን በማስመልከት በተዘጋጀው ስነስርዓት ከኦሮሚያ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም