ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ህንድ አገር ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

69
ኢዜአ ፤ጥር 3/2012 የቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ህንድ አገር ከሚገኘው “ኢንድራ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ” ጋር በድህረ-ምረቃ የርቀት ፕሮግራም ያስተማራቸውን 41 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው እ.አ.አ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ከ“ኢንድራ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ” ጋር በፈጠረው የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነት የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን ለዜጎቹ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል። የቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንደሰን ታምራት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በትብብሩ ከተወሰኑ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሲሰጥ የነበረውን ድጋፍበማስፋትና የዜጎችን ፍላጎት መሠረትተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ይህም በአገራችን የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛው የድህረ-ምረቃፕሮግራም የመማር ዕድል ላላገኙት  ዜጎች ተደራሽ እንዲሆኑ አግዟል ብሏል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም ትብብሩ በሀገራችን በብዛት የማይሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞችን ጨምሮ በተለይም በርቀት ፕሮግራም በስፋት ተደራሽ ያልሆኑትን ያካተተ እንደሆነ የጠቆሙት። በዚህም በንግድ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ቢዝነስ፣ ፖለቲካ፣ በማህበራዊ ስርዓተ-ትምህርቶችየተዘጋጁ ፕሮግራሞች ስምምነቱ ካካተታቸው ፕሮግራሞች ውስጥ ይገኙበታል። በተለይም ህንድ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉት የአለም ሀገራት ምሳሌ መሆኗ ለስምምነቱ መነሻ እንደነበር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታውሰዋል። አገሪቷ ያላ ተሞክሮ በሀገራችን ብቻ ሳይወሰን ለአለምም ጥሩ ተሞክሮ ምሳሌነቷን በመጠቀም የአገራችንን የትምህርት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግና የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመቅሰምም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ወደፊትም የድህረ-ምረቃፕሮግራሞችን ጨምሮ በ3ኛ ዲግሪም ፕሮግራሞችን ለማስፋት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይኸ ምረቃ ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ እና ኢንድ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የትብብር ማዕቀፍ ካደረጉ 10ኛው የምረቃ ፕሮግራም ነውም ተብሏል። በዚህም በ253 ተማሪዎች የጀመረው አሁን ላይ እያደገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን 2 ሺህ 131 ተማሪዎችን በ8 የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም በመስጠት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም