ኢጋድ በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ

81
አዲስ አበባ ሰኔ17/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተዘጋጀው ሰልፍ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ፍንዳታ ጥቃት ያሳዘነው መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ላመጡት ለውጥ ዕውቅና ለመስጠትና ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጀው ሰልፍ ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ150 በላይ ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ይታወቃል። ኢጋድ ለኢዜአ በላከው የሃዘን መግለጫ እንዳመለከተው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ በወጡት የሰልፉ ተሳታፊዎች ላይ የተፈፀመውን ድርጊት በጽኑ አውግዞታል። የኢጋድ ዋና ጸሃፊ አምባሳደር ኢንጂነር ማህቡብ ማሊም ''ሰላማዊ በሆነ መንገድና ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው የፖለቲካ መሪያቸውን ለመደገፍ አደባባይ በወጡ ንጹሃን ላይ የተፈጸመው ጥቃት እጅግ አስደንጋጭ ነው'' ብለዋል። ''በድርጊቱ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽኩ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ'' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ዋና ጸሀፊው በኢትዮጵያ የመጣው አንድነት፣ ዴሞክራሲና ልማት ለአህጉሩና ለቀጣናው ምሳሌ የሚሆን እንደሆነ ጠቅሰዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም