በግድቡ ያደረግነው ጉብኝት አገራዊ ስሜት ፈጥሮልናል-ተማሪዎች

72
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ፅናት የተማሩበትና የተሻለ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑን ተማሪዎች ገለፁ። ይህንን የገለፁት በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡና ሰሞኑን የግድቡን ግንባታ ሂደት የጎበኙ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ግድቡን የጎበኙት ከመላው አገሪቱ የተውጣጡት እነዚህ ተማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት ዕድሉን አግኝተው ቦታውን በማየታቸው ስለግድቡ ተጨባጭ መረጃ እንዲኖራቸው ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር የመፍጠር አቅም እንዳላት እንዳረጋገጠላቸው ተናግረዋል። ጉብኝቱ ስለግድቡ ግንባታ ሂደት በመገናኛ ብዙሃን ከሚከታተሉት በላቀ መልኩ ሰፊ እይታ እንደፈጠረላቸው ተማሪዎቹ ጠቅሰዋል። ግንባታውን እውን ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ የሚታየው ጥረትም ለትውልድ ፅናትን ያስተምራል፤ በመሆኑም በተለይ የአካባቢውን ፈታኝ የአየር ፀባይ ተቋቁመው እየሰሩ የሚገኙ ባለሙያዎች ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል። ተማሪ ፅዮን ጌታቸው እንዳለችው በቦታው በጽናት መስራታቸው የሚበረታታና ለወደፊት ለሚፈልጉ አላማዎች እንዲንወስን አድርጎናል ብላለች፡፡ ተማሪ ያሲን አብዱልከሪም በበኩሉ በቦታው ደርሶ ለማየት በጣም መጓጓቱን ገልጾ ሙቀቱን ተቋቁመው የሰሩት ሰራተኞች ጀግኖች ናቸው፤ ላመሰግናቸውም እፈልጋለ፤ሁ ብሏል፡፡ ተማሪ ማሪያ አስገድ ግንባታውን ማየታችን ለሀገራችን በተገቢው የሚሰሩ እንዳሉና ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን አድርጎናል ብሏል፡፡ በግንባታው በተለያየ ሙያ የተሰማሩት ኢትዮጵያዊያን እያሳዩት ያለው ፅናት ታዳጊ ወጣቶች ለአገራቸው ከዚህ የተሻለ ተግባር እንዲያልሙና በበለጠ አገራዊ ኃላፊነትን እንዲነሳሱ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ የመላው ኢትዮጵያውያን ንብረት በመሆኑ ያልተቋረጠ ድጋፍና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባልም ብለው፤ እስካሁን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል። በትምህርታቸን የተሻለ ውጤት አምጥተን ለወደፊት በተለያዩ ዘርፎች ላይ በግድቡም ሆነ ለተለያዩ የአገራችን ልማቶች የራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባን ይሰማኛልብላ የገለጸችው ተማሪ ሱመያ መሃመድ ናት፡፡ ተማሪ ታጁር አብዱላቲፍ እንዳለው ለአገሬ ነገ ከዚህ የበለጠ ስራ እንድሰራ በውስጤ እንዲቀረፅ አድርጎታል ብሏል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር እንዳሉት የጉብኝቱ ዓላማ ተማሪዎች በአገሪቱ በሚካሄዱት የተለያዩ የልማት ሥራዎች ውስጥ ወጣቶች ተሳታፊ የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚያሰችል ግንዛቤን መፍጠር ነው። ተማሪዎቹ የግድቡ ፕሮጀክት አምባሳደር ሆነው በሌሎች ዘንድ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ማስቻልም የጉብኝቱ ሌላ ግብ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ጉብኝቱ በተማሪዎቹ መካከል የእውቀትና የልምድ መለዋወጥ ዕድል ለመፍጠርም እንደሚያስችል ወይዘሮ ፈቅርተ ገልፀዋል። ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዘው በሚካሄዱት የችግኝ ተከላ፣ አፈር እቀባ ሥራና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ላይ ተማሪዎች በንቃት እንዲሳተፉም ወይዘሮ ፍቅርተ ጥሪ አስተላልፈዋል። ተማሪዎቹ በነበራቸው ቆይታ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ወደባህርዳር በማምራት ጢስ አባይንም ጎብኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም