የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መሥመር ደህንነት ለመጠበቅ መረባረብ ይገባል-የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ

133

 ኢዜአ ጥር 1 / 2012 የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መሥመር ደህንነትን ጥበቃ በማጠናከር ዘርፉ በብልጽግና ጉዞ አሻራውን እንዲያሳርፍ መረባረብ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስገነዘቡ

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሐዲድ ደህንነት ቀን በድሬዳዋ  ተከብሯል።

ምከትል ከንቲባው አህመድ መሐመድ ''ለደህንነታችን ባቡራችን እንውደድ!'' በሚል መሪ ሐሳብ በተከበረው በዓል ላይ እንዳስገነዘቡት ከከተማ ህልውና ጋር የተያያዘውን ባቡር ደህንነት ማስጠበቅ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ለከተማዋ ምስረታና ለሁለንተና ዕድገቷ ባቡር ታላቅ አበርክቶ ነበረው ያሉት አቶ አህመድ፣አሁን በአዲስና ዘመናዊነት የተገነባው የባቡር መሥመር ለድሬዳዋና ለአገሪቱ የብልጽግና ጉዞ መሠረታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

ከተማዋን የምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።

ከአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ ከ90 በመቶ በላይ የሚመላለስበትንና ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘውን መሥመር በተቀናጀ መንገድ ለመጠበቅ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ታን ጂአን በበኩላቸው ባቡር ለኢትዮጵያና ለድሬዳዋ ብልጽግና ዋና መድረሻ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቻይናና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ግንሹነት ከማጠናከር በዘለለም ለኢትዮጵያና ለድሬዳዋ ማበብና መልማት ሁነኛ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ መንቀሳቀሻ ከሆነው የጅቡቲ ወደብ ጋር መገናኘቱ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለኢንዱስትሪ እድገት እንዲሁም ባቡር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎችና ወጣቶችን ህይወት በመለወጥ ድርሻ እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመሠረተ ልማቱን አመቺነት በመገንዘብ የቻይና ባለሃብቶች በከፍተኛ ደረጃ እየመጡ ይገኛል ያሉት አምባሳደሩ፣ ዘርፉ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እንዲያሳካ አገራቸው ድጋፏን ታጠናክራለች ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መንገሻ ሞላ በበኩላቸው የባቡር መሥመሩ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውንና የብልጽግና ጉዞው እንዲሳካ ሁሉም ለአስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የፌደራልና ባቡር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አካላት፣ ነዋሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ለባቡር ደህንነት መረጋገጥ እያበረከቱ ላለው ተግባር አመስግነዋል።

ደህንነቱን ለመጠበቅ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ሳርካ በበኩላቸው የኢትዮጵያ፣የጅቡቲና የቻይና መንግሥታት ተቀናጅተው የዘረጉትን ዘመናዊ የባቡር መሥመር የሚያልፍባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰብ ክፍሎች ደህንነቱን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።

የባቡሩን የመሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለማንቀሳቀስና ለመጠገን የቻይና ባለሙያዎች ለስድስት ዓመታት  እንዲያንቀሳቅሱትና እውቀታቸውን ለኢትዮጵያውያንና ለጅቡቲያውያን እንዲያስተላልፉ ስምምነት መደረሱንም አስታውቀዋል፡፡

ቀኑን ምክንያት በማድረግ  በመልካጀብዱ ፣በሽንሌ ፣ በሚኤሶ፣ ቦርደዴና በመተሃራ ለሚገኙ 90 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና የስፖርት መጫወቻዎች በስጦታ ተበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም