ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደረግ የአስር ዓመት ረቂቅ የልማት እቅድ ተዘጋጀ

124

 ኢዜአ ጥር 01/2012፡- ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቀጣይ አስር ዓመት ረቂቅ የልማት እቅድ ማዘጋጀቱን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከዘጠኝ የኢኮኖሚ ሴክተር ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላትና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር እቅዱን ለማዳበር የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

መድረኩ ዛሬ በተጀመረበት ወቅት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር  ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተይቷል።

ሆኖም አሁንም ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉና በተለይም የወጣቶች የሥራ አጥነት ቁጥር እየጨመረ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛና የውሳኔ ሰጪነት ድርሻቸውም  በመንግስት መዋቅር ዝቅተኛ በመሆኑ ወቅቱን ያገናዘበ  የልማት እቅድ ማዘጋጀት መስፈለጉን አመልክተዋል።

"ረቂቅ የልማት እቅዱ በዘርፉ ያሉትን  ችግሮችን ከመሰረቱ በመፍታት የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከ50 በመቶ በላይ በማሳደግ ሀገሪቱን  ወደ ብልፅግና ጎዳ የሚወስድ ነው "ብለዋል።

እንደሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ መድረኩም ከክልል አመራሮችና የኢኮኖሚ ሴክተሮች፣ ከፌዴራል ተቋማትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር እቅዱን ለማዳበርና የማስፈፀሚያ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተዘጋጀ ነው።

በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የሴቶችና ወጣቶች ማካተት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አሸናፊ ፈይሳ በበኩላቸው የሥራ እድል ፈጠራ፣ሴቶችን በኢኮኖሚና የማስፈፀም አቅም ማብቃት፣በሁሉም መስኮች የስርዓተ ፆታ እኩልነት ማረጋገጥ የእቅዱ ዋነኛ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

"እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመጠቀም  ለማስፈፀሚያ የሚረዱ ጥናቶች፣ መመሪያዎችና ስልቶችን እያዘጋጀን ነው" ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ፣ በሥራ እድል ፈጠራና በሌሎችም የኢኮኖሚ መስኮች ከ10 ሚሊዮን በላይ  ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የሴቶች ተሳትፎ 30 በመቶ እና የወጣቶች ተሳትፎ ደግሞ 70 በመቶ እንደሆነ  አቶ አሸናፊ አመልክተዋል።

በቀጣይ አስር  ዓመታት አሁን ያለውን ውጤት ከመሰረቱ የሚቀይር የልማት ሥራዎች በዘርፍ ለማከናወን ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም  አብራርተዋል።

መድረኩ  ለሁለት ቀናት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም