ህንድ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የነጻ የትምህርት እድል ይፋ አደረገች

127
ኢዜአ፤ ጥር 1/2012 ህንድ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የ''2020 '' ነጻ የትምህርት እድል ይፋ አደረገች። ህንድ ለሁለተኛ ጊዜ በሰጠችው የነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለመሆን ከስድስት ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ተመዝግበዋል። ምዝገባውን ላደረጉት ተማሪዎች ዛሬ በአዲስ አበባ የህንድ ኤምባሲ በኩል ገለጻ ተደርጓል። ምዝገባው የህንድ መንግስት ባዘጋጀው የድረ-ገጽ አድራሻ ላለፉት ወራት የተካሄደ ሲሆን፤ መርሃ ግብሩ አገር አቀፍ የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ጨምሮ ለመጀመሪያ ዲግሪ፣ ለድህረ-ምረቃና ለሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚሰጥ ነው። በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሚስተር አኑራግ ስሪቫስታቫ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያና ህንድ በትምህርት ብቻ ከ2 ሺ 500 ዓመት በላይ የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል። የነጻ ትምህርት እድሉ በህንድ መንግስት ተነሳሽነት የሚሰጥ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ወደ ተግባር ገብቶ ከ300 በላይ ተማሪዎችን  የእድሉ ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል። የ''እስተዲ ኢን ኢንዲያ ፖርታል'' ዋና አስተባባሪ ሚስተር አሹቱሽ ኩማር በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ የተሰጠው ኮታ 25 በመቶ ሲሆን፤ 3 ነጥብ 2 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡና የእድሉ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ተማሪዎች መመዝገባቸውን አውስተዋል። ''እስተዲ ኢን ኢንዲያን ፖርታል'' የተሰኘው ይህ የነጻ የትምህርት እድል ተማሪዎቹ የመግቢያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ህንድ ካሏት 30 ሺ በላይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በ116ቱ መስፈርቱን የሚያሟሉ ተማሪዎች በፍላጎታቸው መሰረት እንደሚመደቡ ገልጸዋል። ተማሪዎቹ በጥር የሚፈልጉትን ዩኒቨርሲቲ እንዲመርጡ፣ ጥሪ የተደረገላቸው ደግሞ በሚያዚያ ፈተና እንዲወስዱና በሰኔና ሃምሌ ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚጀምሩም ተገልጿል። ከ2 ሺ 600 በላይ የትምህርት ዓይነቶች የሚካተቱበት መረሃ ግብር ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች የሚሰጥ ነው። የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑት ዜጎች ከትምህርት ባሻገር የአገራቷ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያበረክቱት ሚና የጎላ እንደሆነ ዋና አስተባባሪው አክለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም