የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለዶክተር ዐቢይ አህመድ ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ

2432

ጅግጅጋ/ ሐረር ሰኔ17/2010 የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እያስመዘገቡ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ትናንት በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንደሚያወግዘውም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የሐረሪ ሊግ አባላትና ደጋፊዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅናና ድጋፍ ለመስጠት ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት በመድረሱ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ዛሬ ጠዋት በጅግጅጋ ስታዲየም በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ በጅግጅጋ ከተማ ከሚገኙ 20 ቀበሌዎችና ከአካባቢው ወረዳዎች የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 17 ነዋሪ አቶ ዘከሪካ አብዲራዛቅ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ እየታየ ያለውን የፖለቲካ ለውጥና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፍ ለመስጠት ሲሉ በሰልፉ ላይ መታደማቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት አገሪቱ ወደ ሰላምና መረጋጋት እየመጣች መሆኗን ገልጸው፣ በቀጣይም የጀመሩትን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።

ለለውጥ እንቅስቃሴያቸው ውጤታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

በከተማው የቀበሌ 06 ነዋሪዋ ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የሆነና ህዝቡን ወደ አንድ የሚያመጣ አመራር በማግኘቷ ለአመራሩ ያላቸው ምስጋና ለመግለፅ ሲሉ በሰልፉ ላይ መታደማቸውን ገልጸዋል፡፡

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲጎለብት፣ ሙስና እንዲጠፋና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አበክረው እንዲሚሰሩ በተለያየ መድረክ መግለጻቸው ከልብ አስደስቶኛል” ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ላለው ታላቅ ለውጥ ድጋፍ ለመስጠት በሰልፉ ላይ መገኘታቸውንና በቀጣይም ለለውጡ ስኬት ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ የገለጹት ደግሞ ከቀብሪ በያህ ወረዳ የመጡት አቶ ኒምዓን ዩኒስ ናቸው፡፡

በጅግጅጋ ስታድየም በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ በበኩላቸው ትናንት በመስቀል አደባባይ በተደረገው የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

በጥፋት ኃይሎች በንጹሃን ዜጎች ሕይወትና አካል ላይ በደረሰው አደጋ የክልሉ መንግስትና ህዝብ በእጅጉ ከማዘናቸው በላይ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል፡፡

በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ቤተሰቦች መጽጽናናትንም ተመኝተዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ለተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ለመስጠት ሰልፉ ላይ ለተገኙ የጅግጀጋ ከተማና አከባቢዋ ነዋሪዎች ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጅግጅጋ ስታዲየም ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ነዋሪዎቹ ዶክተር አብይንና የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር የሚያወድሱ የተለያዩ መፈክሮችን በማንገብና ቲሸርቶችን በመልበስ ለሁለቱ መሪዎች ያላቸውን ድጋፍ አሰምተዋል፡፡

ለሰዓታት በቀጠለው የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ፖሊስ ሙዚቃ ባንድ የህዝቡን አንድነት የሚያንጸባርቁ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ያዝናና ሲሆን ሰልፉም በሰላም ተጠናቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ዶክተር ዐቢይ አህመድ ላከናወኗቸው ተግባራትና የለውጥ እንቅስቃሴዎች ድጋፍና ምስጋና ለማቅረብ በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት በተዘጋጀ ሰልፍ በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት መድረሱ እንዳሳዘናቸው የሐረሪ ሊግ አባላትና ደጋፊዎች ተናገሩ።

የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ዛሬ በሐረር ከተማ በሚገኘው አሚር አብዱላሂ መሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄዱት ውይይት ላይ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዝን ገልጸዋል።

በሀዘን መግለጫቸው ላይ እንዳመለከቱት በንጹሃኑ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር በመሆኑ በጽኑ እንደሚያወግዙት አመልክተዋል።

ለተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።

በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች በተጠናከረና ህዝባዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንደሚቀጥሉም የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ሊቀመንበር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ በበኩላቸው መንግስት የጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ፣ እውቅናና ምስጋና ለመስጠት በወጡ ዜጎች ላይ ትናንት በደረሰው የቦምብ አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

ድርጊቱ የትኛውንም ብሔር የማይወክል፣ የከሰረ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውና ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት የፈጸሙት መሆኑን ነው የገለጹት።

ልዩነት ቢኖር እንኳ በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ሲቻል በንጹሃን ዜጎች ላይ የሕይወትና የአካል ጉዳት ማድረሳቸው  ፍጹም እንዳሳዘናቸውና ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

አጥፊዎች በቀጣይ ከእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር እንዲታቀቡም አስገንዝበዋል።

የሐረሪ ብሔራዊ ሊግም ከህዝቡ ጋር የጀመረውን የልማት፣ የሰላምና የለውጥ ስራ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በከተማው በሚገኘው አሚር አብዱላሂ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው መድረክ ከአንድ ሺህ በላይ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።