ለውጥን ደግፈው አደባባይ በወጡ ንጹሐን ላይ የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን...የኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ነዋሪዎች

69
አምቦ/ፍቼ/ነጌሌ/መቱ/ጅማ/ነቀምቴ/ጎባ17/2010 የጠቅላይ ሚኒትሩን የለውጥ ጅምር በመደገፍ በመስቀል አደባባይ በተገኙ ንጹሐን ላይ ጥቃት የፈጸሙ ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጠየቁ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአምቦ ፣ ፍቼ ፣ ነገሌ ቦረና ፣ መቱ ፣ ጅማ ፣ ነቀምቴና ጎባ ከተሞች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ድርጊቱ አረመኔያዊና ለውጡን ለማደናቀፍ በመሆኑ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል። የአምቦ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አብዲሳ በንቲ "ጥቃቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት የለውጥ ጎዳና የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከጎናቸው በፅናት እንድንቆም  እልህና ወኔ  የምንታጠቅበት እንጂ በፍፀም አያንበረክከንም" ብለዋል ። አቶ ፍቃዱ ቤኩማ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "ፍቅራችን፣ሰላማችንና አንድነታችን በሽብር ጥቃት እንደማይቀለበስ የውስጥም ሆኑ የውጭ ጠላቶቻቸን በሚገባ አልተገነዘቡትም" ብለዋል። የተፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊትም ትግሉ የበለጠ እንዲጠነክር የሚያደርግ እንጂ ወደ ኋላ የማያስቀረው እንደሆነ አስረድተዋል። የፍቼ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ በላይ ንጉሴ  በበኩላቸው "የኢትዮጵያን  አንድነት ለትውልድ ለማስተላለፍ ይቅርታ ፣ፍቅርና መተባባርን የሰበከውን ሰልፍ ለማደናቀፍ የተፈጸመው ጥቃት ጸረ-ህዝብ ድርጊት በመሆኑ እናወግዘዋለን" ብለዋል። የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪ አቶ በነበሩ ደምሴ በተመሳሳይ እንደገለጹት ሰላማዊ ሰልፉ ኢትዮጰያውያን  በፖለቲካ ፣በዘርና በብሄር ልዩነት ተከፋፍለዋል የሚለውን የተሳሳቱ አመለካከቶችን የሰበረ ነው ። "ይህንኑ የተቀደሰ ዓላማ በሚያራምዱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት ሰይጣናዊ በመሆኑ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል" ብለዋል ። የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው አቶ ተስፋዬ ጽጌ ደግሞ ጥቃቱ ሰላም ፣ ልማት ፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና መፈቃቀራችንን በማይፈልጉ ሃይሎች የተቃጣ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንታገለውና ልናወግዘው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ። በጅማ ከተማ የቆጪ አካባቢ ነዋሪው አቶ አበበ ዓለማየሁ እንደገለፁት ጥሩ የሰራን ማመስገን የሚደገፍ እንጂ ለጥቃት መንስኤ እንደማይሆን በመግለፅ "ድርጊቱ እንዳይደገም አስተማሪ እርምጃ መወሰድ አለበት"።ብለዋል። በመቱ ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ባንቻየሁ ታምሩ እንዳሉት ሰላም ፣አንድነት ፣ፍቅርና ይቅር ባይነት በሚሰበክበት መድረክ ላይ እንደዚህ አይነት ጥቃት መሰንዘር ሀገሪቱን ለማጥፋት ያለመ በመሆኑ አጥብቀው የሚያወግዙት ነው። "የሀገሪቱ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን ያጠናከሩበት ወቅት ነው"  ያሉት ወይዘሮዋ የጥቃቱ ፈጻሚዎች የትኛውንም ብሄር የማይወክሉ ጥቅመኞች እንደሆኑም ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በድርጊቱ ማዘናቸውን በመግለፅ በጥቃቱ የተሳተፉ ሃይሎች በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ የጠየቁ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም