በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች እንዲታረሙ ባለድርሻ አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

347
አዳማ ሰኔ17/2010 በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ህገመንግስታዊ የመብት ጥሰቶች እንዲታረሙ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት እገዛ እንዲያደርጉ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጥሪ አቀረበ። የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሴቶችና በህፃናት ላይ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥሰቶች እንዳያጋጥሙ ቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰቱም ፈጥኖ ማረም በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመምከር ያዘጋጀው ዓውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ እንደገለጹት ህገ መንግስቱ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ በተለይ ደግሞ ለሴቶችና ህጻናት ያጎናፀፋቸው መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ጥረትና እገዛ ያስፈልጋል። ህገ መንግስቱ ጥቅል ጉዳዮችን ያካተተና የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ቢሆንም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ህጎች አፈጻጸም ላይ የሚሰጡት ውሳኔዎች  ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጩበት አጋጣሚ መስተዋሉን ኃላፊው ተናግረዋል ። አቶ ደሳለኝ እንዳሉት፣ ከታችኛው እስከ ላይኛው የፍርድ ቤት ደረጃ አስፈላጊ የህግ ክርክር ተደርጎበት ጭምር ህገ መንግስታዊ የመብት ጥሰት ተፈፅሞብኛል የሚል ቅሬታ ያለው አካል ካለ ለአጣሪ ጉባኤው አቅርቦ ማስመርመር ይችላል። ጽህፈት ቤቱ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን ለማጣራት በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት 2000 ዓ.ም ጀምሮ ከግለሰቦች፣ ከቡድኖች፣ ከተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከማህበራት 3 ሺህ 300 አቤቱታዎች ቀርበውለት ምርመራ ማካሄዱንም ጠቁመዋል ። ከቀረቡለት አቤቱታዎች መካከል 55ቱ የህገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ሆነው ስለተገኙ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፉ መደረጉን አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል ። ጉባኤው ለፌዴሬሽኑ ያስተላለፋቸው አቤቱታዎችና የተሰጡት ውሳኔዎች የህገ መንግስቱን የበላይነት ያስጠበቁ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን በተለይ ደግሞ የህፃናትንና የሴቶች መብቶችን ያስከበሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የህዝብ ሀብት መሆኑን ያረጋገጡ፣ አርሶአደሮች ከእርሻ መሬታቸው ያለመፈናቀል ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበር ያደረጉ መሆናቸውን ነው የገለጹት። "ንብረት የማፍራትና ሌሎች ህገመንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ ለህገ መንግስቱ እድገት የጎላ ድርሻ ያላቸው ውሳኔዎች ነበሩ" ብለዋል ። "በህገ መንግስት ጥሰት ከቀረቡ አቤቱታዎች አብዛኛዎቹ በሴቶችና ህጻናት ላይ ያተኮሩ ናቸው" ያሉት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የህገመንግስት ተመራማሪ ወይዘሮ ራሄል ብርሃኑ ናቸው ። ቅሬታቸውን ያቀረቡት አንጻራዊ አቅም ያላቸው ሴቶችና እገዛ ያገኙ ህፃናት ብቻ መሆናቸውን ተመራማሪዋ ጠቁመው በአቅም ማጣት ምክንያት  የከፋ የመብት ጥሰት ደርሶባቸው ወደ ጉባኤው መቅረብ ያልቻሉ በርካቶች መሆናቸውን አስረድተዋል ። እንደ ወይዘሮ ራሄል ገለጻ በህጻናት ላይ የሚደርሱ የህግ ጥሰቶች በአባትነት የመጠሪያ ስምና በወራሽነት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በሴቶች ላይ ደግሞ ከሀብት ማፍራትና ከንብረት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ የእኩልነት መብት ጥሰቶች ናቸው። በሴቶችና ህፃናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚደርሱ ህገመንግስታዊ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን አውቀው የራሳቸውን እገዛ ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ የክልልና የፌዴራል መንግስት የሴቶችና የህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች፣ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ። በመድረኩ ላይም የሴቶችና ህጻናት መብቶች በዓለም አቀፍና በኢፌዴሪ ህገመንግስት እንዲሁም ሴቶችንና ህጻናትን አስመልክቶ በአጣሪ ጉባኤውና በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተወሰኑ የተመረጡ ጉዳዮች ላይ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በተጨማሪም በፍቺና ከአንድ በላይ ጋብቻ በሚኖርበት ጊዜ በፍርድ ቤቶች የሚደረግ የንብረት ክፍፍል ውሳኔ ከህገ መንግስት አንጻር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊዎቹ እንደሚመክሩ ተመልክቷል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም