በሰላማዊ የድጋፍ ሰልፉ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የደም ልገሳ ተደረገ

87
ሰኔ 17/2010 ትናንት የአዲስ አበባና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለታዩ ለውጦች እውቅና ለመስጠትና ምስጋና ለማቅረብ ባካሔዱት ሰላማዊ ሰልፍ  ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖች በደም እጥረት ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የደም ልገሳ እየተካሄደ ነው፡፡ “ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ከ150 በላይ የሚሆኑት ቀላልና ከባድ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ  በብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ተገኝቶ  ያነጋገራቸው ደም ለጋሾች እንዳሉት በአደጋው  የተጎዱ ወገኖች በደም እጥረት ተጨማሪ ጎዳት እንዳይደርስባቸው በማሰብ ነው ደም ለመለገስ የተገፋፉት፡፡ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው የኦሮሚያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ ፈቲያ መሃመድ በትናንቱ የቦምብ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የደም እጥረት እንዳይገጥማቸው በማሰብ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ደም ሲለግሱ የመጀመሪያቸው መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ህይወትን ለማትረፍ ደም መለገስ አስፈላጊ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ሀብት አስተዳደር የስራ ኃላፊው  አቶ ልጃለም ያለው  ደም የህይወት ምንጭ በመሆኑ ካሁን በፊትም ደም እንደሚለግሱ ገልጸው ዛሬ ደም ለመስጠት ያነሳሳቸው ግን  ትናንት የተከሰተው አደጋ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሌላዋ ደም ለጋሽ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ኃላፊ ወይዘሮ  ጫልቱ ሰኒ በትናንቱ የድጋፍ ሰልፍ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በደም እጦት ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉ ደም ለመስጠት መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመከላከያ እስፖርት ክለብ የእጅ ኳስ ተጫዋቹ  ሃምሳ አለቃ  ጥላሁን ሲሳይም  ደም የመለገስ ልምዱ ቢኖረውም ዛሬ በቦታው የተገኘበት ምክንያት ግን በድጋፍ ሰልፉ ላይ የደረሰው አደጋ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ በድጋፍ ሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የደም እጥረት መኖሩን ሰምቶ ደም ለመስጠት መምጣቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት ምንያህል ታደለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገበያና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሚኪያስ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት  ብሔራዊ የደም ባንኩ በድጋፍ ሰልፉ  ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ ለቀረበለት የ200 ዩኒት ደም ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዛሬ ህብረተሰቡ ማንም ሳይቀሰቅሰው ደም ለመለገስ ወደ ብሔራዊ ባንኩ ባይመጣ ኖሮ በወጣው ደም ልክ ተተኪ እስከሌለ ድረስ እጥረት ሊያጋጥም ይችል እንደነበርም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ትናንት የደረሰውን አደጋ ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት  በርካታ ሰዎች ያለማንም ቀስቃሽ ደም እየሰጡ መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ ብሔራዊ የደም ባንኩ ከተመሰረተ ጀምሮ በየጊዜው የህብረተሰቡ ደም የመለገሰ ባህል እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም የደም ፍላጎትና አቅርቦቱን ተመጣጣኝ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው አቶ ሚኪያስ የገለጹት፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም