ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ114 ተማሪዎች ፣ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

83

ኢዜአ ታህሳስ 30/ 2012  የመማር ማስተማር ስራን አስተጓጉለዋል ባላቸው 114 ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና የሰራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የጅማ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርስቲው የውጭ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በተቋሙ አለመረጋጋት እንዲፈጠርና የመማር ማስተማር ስራውን እንዲስተጓጎል ያደረጉ 51 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ከእነዚህም 20ዎቹ ከአንድ ዓመት እስከ መታገድ እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው።

ቀሪዎቹ ተማሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ሰፊ ግምገማ በስራቸው ላይ ድክመት ያሳዩት 29 የጥበቃ ሰራተኞች ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉን ዶክተር አሸናፊ  ጠቅሰዋል።

ሌሎች 28 የጥበቃ ሰራተኞች ደግሞ በጡረታ መገለላቸውን  አስታውቀዋል።

በተለያዩ የአስተዳደር ደረጃዎች ያሉ ሶስት የቢሮ ኃላፊዎች በሌላ እንዲተኩ መደረጉን የገለጹት ዶክተር አሸናፊ በአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዙሪያ የምክትል ፕሬዝዳንትና የሶስት ዳይሬክተሮች ለውጥ መካሄዱንም አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከማህበረሰቡና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ለሁለት ወር ባደረገው ውይይትና የማጣራት ስራ እርምጃውን ወስዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም