በጋምቤላ የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እንዳላገኙ ነዋሪዎች ገለጹ

64
ኢዜአ ታህሳስ 29/2012 ፡- በጋምቤላ ከተማ በህዝቡ ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እንዳላገኙ ነዋሪዎች ገለጹ። የክልሉ ምክር ቤት አባላት በጋምቤላ ከተማው ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሄደዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ኑኑ ኡጉድ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በከተማው ህዝብ ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር  ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የምክር ቤት አባላት ያደረጉት ጥረት ውስን ነው። አባላቱ ከለውጡም በፊት ሆነ  በኋላ የመራጣቸውን ህዝብ ቅሬታ በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት ያደረጉት ጥረት ዝቀተኛ እንደሆነም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ያልተፈቱት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን የሰላም ችግር ጭምር እንደሆነ  የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዘመድአገኘሁ ጋረድ ናቸው። "አሁንም ቢሆን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከተፈለገ ሁሉም በቅድሚያ ለሰላም መስራት አለበት" ብለዋል። አቶ ዲድሙ አበላ የተባለት ነዋሪ በበኩላቸው "የጋምቤላ ከተማ ካለበት የመሰረተ ልማት ችግር አኳያ አይደለም የክልል ከተማ ቀረቶ ለወረዳ የሚመጥን አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በከተማው የጋምቤላ ስታዲዬምን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረው  በሙስና ችግር ሳይጠናቀቁ በመቅረታቸው መፍትሄ እንዲያገኙ  የምክር ቤት አባላት ክትትል በማድረግ መስራት እንዳለባቸውም  አመልክተዋል። አስተያየት ሰጪዎች በመንግስት ለህዝቡ የሚቀርቡ የፍጆታ ሸቀጦች  የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆኖ እንደቀጠለ ጠቁመው ይህም  የምክር ቤት አባላት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ባለማድረጋቸው እንደሆነም ገልጸዋል። የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ኡጁሉ ጊሎ በነዋሪዎቹ የተነሱት  ጥያቄዎችን በተቻለ አቅም ለመመለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። ሆኖም  ሁሉንም የልማት ፍላጎት በተወሰነ ጊዜ ለመመለስ የበጀት አቅም ስለሚወስን ክፍተቶች መኖራቸውን አስረድተዋል። በተለይም በመንግስት ከሚቀረቡ የስኳርና ሌሎች የፍጆታ ሸቀጦች ተያይዞ የተነሱት ጥያቄዎች አግባብነት እንዳላቸው አምነው የማስተካከል ስራ መጀመሩን ጠቁመው " ለስኬታማነቱ የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አታርፋ ምስጦፋ  በበኩላቸው  በከተማው ተጀመረው የቆሙትን የልማት ፕሮጀክቶች   የምክር ቤቱ አባላት አስፈላጊውን ክትትል ስራዎችን እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። የምክር ቤቱ አባላት ባለፈው  ጉባኤ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የቀረቡለትን የአፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውሰው" በቀጣይም የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል "ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቀጣይ ምላሽ እንዲያገኙ ሁሉንም አካላት ባሳተፈ  መልኩ እንደሚሰራ ሌላው  የምክር ቤት አባል  ወይዘሮ አለሚቱ እሞድ ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤት የመስክ ምልከታና  ውይይቱን ያዘጋጀው በህዝቡ የተነሱ ችግሮችነ በመለየት የእርምት እርምጃ ለመውሰድ እንደሆነም አስረድተዋል። የክልሉ ምክር ቤት አባላት በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር  ለስምንት ቀናት ሲያካሂዱ የቆዩት የመስክ ምልከታና ህዝባዊ ውይይት አጠናቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም