በጤናው ዘርፍ የሚካሄዱ ምርምሮች ለጤናው ዘርፍ መሻሻል አስተዎጽኦ እያደረጉ አይደለም ....የዘርፉ ምሁራን

69
ባህር ዳር ሰኔ 17/2010 በጤናው ዘርፍ የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች የተመራማሪዎችን ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ ለጤናው ዘርፍ መሻሻል አስተዎጽኦ እያደረጉ አለመሆኑን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ። የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉበዔ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በጉባዔው ላይ የተሳተፉት ምሁራን እንደገለጹት በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሰረቱና የሰዎችን ደረጃ ለማሻሻል ብቻ የሚከናወኑ ናችው። ይህም በመሆኑ በጤናው ዘርፍ ላይ በርካታ የምርምር ሥራዎች ቢካሄዱም ከመደርደሪያ አልፈው የሚፈለገውን ውጤት እያስገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ምርምር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈንታሁን ቢያድግልኝ እንደሚሉት በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ምርምሮች የሰዎችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ አይደሉም። የአገሪቱ የጤና ዘርፍ እንዲሻሻልና ለህብረተሰቡ ችግር ፈች የሆኑ ምርምሮች እንዲካሄዱ በዘርፉ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ምሁራን በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ምርምር ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የባህር ዳር ጤና ሳይንስ ኮሌጅም በምክንያት ላይ የተመሰረቱ የምርምር ሥራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑን እስገንዝበዋል። እንደ አገር በጤናው ዘርፍ ላይ የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች የሕብረተሰቡን የጤና ችግር ከግምት ያላስገቡና ተመራማሪውን ለማሳደግ ብቻ ታልመው የሚሰሩ በመሆናቸው ለውጥ እየመጣ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋምቢ ጠቅላላ ቲችንግ ሆስፒታል ስፔሻሊስት ኃኪምና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ናቸው። ችግር ፈች ምርምሮችን ለማድረግና ለሕብረተሰቡ ጤና መሸሻል የሚጠቅሙ ስራዎችን ለማከናወን ምሁራን ወደ ራሳቸው መመልከትና ትኩረት የሚሹ የጤና ጉዳዮችን በመለየት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመላክተዋል። የኢትዮጵያን የጤና ችግር ለመፍታት ለራስ የሚመችን ርዕስ መምረጥ ሳይሆን ከህብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የአገሪቱን የጤና ችግር መሰረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም " ጠቁመዋል የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች ውጤት እንዲያመጡ የክልሉ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የምርምር ማዕከል ማቋቋሙን ገልጸዋል። ለክልሉና ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆነ የተደራጀ የምርምር ውጤትን አደራጅቶ ለመያዝ የሚያስችል ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርአትም እየተገነባ መሆኑን ነው ያስረዱት። በትናንትናው እለት በክልል ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው በምርምር የተደገፈ የድንገተኛ ጊዜ የሕክምና መስጫ ቤተ-ሙከራም ተመርቆ ለሥራ ክፍት ሁኗል። ለሦስት ቀን በቆየውና ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው የምርምር ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የፌዴራልና የክልል የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም