በሰልፈኞች ላይ የተፈጸመው እኩይ ተግባር በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ ነው ...የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች

78
ሀዋሳ ሰኔ 17/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለድጋፍ ሰልፉ በወጡ ዜጎች ላይ የተፈፀመው እኩይ ድርጊት በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ አጸያፊና ከኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች አወገዙ ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ያስተላለፉት መልዕክት ዘረኝነትና ጥላቻን በማጥፋት ፍቅርና ቅንነት በልባቸው እንዲነግስ ማድረጉንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ማርታ በሀይሉ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው፡፡ "ብሔራዊ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲያድግና እንዲበለጽግ ምክንያት ሆነዋል" ብለዋል፡፡ ወደስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ባሳዩት አገራዊ ፍቅር፣ በወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎችና ይቅር ባይነት አስተሳሰባቸው ኢትዮጵያ ገብታ ከነበረችበት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ መንገድ የከፈቱ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመስቀል አደባባይ በተካሄደ ሰልፍ ላይ በተፈፀመው የክፉዎች ድርጊት ማዘናቸውን ገልፀው ድርጊቱ ህዝቡን ከሳቸው ጋር ከመሆን፣  ከአንድነት አስተሳሰብና ከመደመር እንደማያግደው ተናግረዋል፡፡ "ዶክተር ዐቢይ በሰልፉ ላይ ያደረጉት ንግግር ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ትልቅነት ለመመለስ ያላቸውን ተነሳሽነት ያየሁበት ነው" ያሉት የከተማው ነዋሪ ደግሞ አቶ ተስፋዬ ማሩ ናቸው፡፡ በእሳቸውና ለድጋፍ ሰልፍ በወጣ ሰላማዊ ህዝብ ላይ በተቃጣው እኩይ ድርጊት የሰዎች ሕይወት ማለፉና የአካል ጉዳት መድረሱ እንዳሳዘናቸውም ገልፀዋል፡፡ "በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ አፀያፊና ከማንም ኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ሰይጣናዊ ተግባር ነው ሲሉም " አቶ ተስፋዬ አውግዘዋል፡፡ በሃዋሳ ከተማ የባጃጅ ሾፌርና የከተማው ነዋሪ ወጣት መላኩ አለማየሁ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር "ሌብነትን፣ ዘረኝነትና ጥላቻን እምቢ በማለት ባለንበት ከጎኑ ለመቆም የሚያነሳሳ ነው” ብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ዘረኝነትና ጥላቻን በማጥፋት ፍቅር፣ ቅንነትና አንድነት በልባቸው የዘራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ "ትናንት በተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት እጃቸው ያለበት አካላት ለህግ ቀርበው በንጹሀን ላይ ለፈጸሙት ተግባር አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቃቱ በኋላ ወዲያውኑ በኢትዮጵያ ቴሌቨዥን ቀርበው መግለጫ መስጠታቸው ምን ያህል ለህዝባቸው እንደሚጨነቁና ለዜጎች ያላቸውን ክብር የሚያሳይ መሆኑን ተናግሯል፡፡ "መግደል መሸነፍ ነው" በሚለው ንግግራቸው መደነቁን የገለጸው ወጣቱ አደባባይ ለወጣው ሰልፈኛ “ክፋትን፣ ጥላቻንና ግድያን ያሸነፋችሁ ትልቅ ህዝቦች ናችሁ” ማለታቸው የህዝቡን ሀዘንና መረበሽ የሚያስረሳ ትልቅ ንግግር መሆኑንም ተናግሯል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የከተማው ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ በተጣለ ቦምብ ለተሰው ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም