የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት በሰልፍ ገለጹ

61
ድሬዳዋ ሰኔ 17/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ላከናወኗቸው ተግባራት "ጥሪህን ሰምተን ተደምረናል" የሚል መልእክት የተላለፈበት ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በድሬዳዋ ከተማ ተካሔደ። የከተማው ነዋሪዎች ዛሬ ማለዳ "እኛ ድሬዎች ጥሪህን ሰምተን ተደምረናል" የሚል የዶክተር ዐቢይ አህመድ ምስል ያለበት ካነቴራ ለብሰው በታላቅ ሰልፍ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች ወደ ስታዲየም የወጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ህብረት፣ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ይበልጡኑ ስለ ኢትጵያዊነት የተናገሯዋቸውን መልዕክቶች የሚያንጸባርቁ በሁሉም ቋንቋዎች የተጻፉ መልዕከቶችን አንግበው ነበር። "ከቃልህ ጋር የሚስማሙ እርምጃዎችህን በመደገፍ አላማህን ለማሳካት እስከ መጨረሻው ከጎንህ ነን የሚሉ መፈክሮችንም" አሰምተዋል ፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ፋናዬ ይመር "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገሪቱ ታላቅ መሆን፣ ለህዝባቸው አንድነትና ፍቅር እየሰሩ የሚገኙትን ተግባር ለመደገፍ እዚህ በመገኘቴ ተደስቻለሁ" ብለዋል ፡፡ ለፍቅር ፣ ለእኩልነት ፣ ለአንድነት ለተሻለች ሀገር ብልጽግና የጀመሯቸውን ተግባራት ለማሳካትም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። ሌላው ተሳታፊ አቶ አሊ ሐሰን አብዶሽ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል መደመራቸውን ለመግለጽ አደባባይ መውጣታቸውን ገልጸው፣ በአዲስ አበባው መስቀል አደባባይ የደረሰው ጥቃት የለውጡን ጉዞ እንደማያደናቅፍ እምነታቸውን አስረድተዋል። በዚሁ አደጋ ለሞቱ እና ለቆሰሉ ወገኖች የተሰማውን ሃዘን በመግለጽ ድርጊቱ የተያዘውን የመደመርና የአንድነት ጉዞ እንደማያደናቅፈው የተናገረው ደግሞ ወጣት ፌይሰል መሐመድ ነው፡፡ ጥቃቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማንኛውም መንገድ ለሚያከናውኑት የለውጥ እንቅስቃሴ የሚደረገውን ድጋፍ ይበልጥ የሚያጠናክር እንጂ ወደኋላ የሚጎትት እንዳልሆነም ተናግሯል። ከ150 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉን ተቀላቅለው ከአራቱም  አቅጣጫ በመትመም ዋና መሰብሰቢያውን ድሬዳዋ ስቴዲየም አድርገዋል፡፡ በስነ ስርአቱ ላይም የከተማው ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን ባስተላለፉት መልዕክት በአዲስ አበባው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸውና ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ማዘናቸውን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል። "ይህ ቀን ህዝብ በገዛ ፈቃዱ የሀገሩን መሪ ሊያመሰግን እውቅና የሰጠበት በመሆኑ ታሪካዊ ቀን ነው" ሲሉም ተደምጠዋል ። ከንቲባው ባስተላለፉት መልእክት "የመደመሩና የለውጡ ጉዞ ሳይደነቃቀፍ ግቡን እንዲመታ እያንዳንዱ ዜጋና ሰራተኛ በተሰማራበት መስክ ውጤት ለማምጣት መትጋት ይገበዋል" ብለዋል። የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወጣት እንድሪስ ተካልኝ የድጋፍ ሰልፉ ለለውጥ፣ ለዲሞክራሲ ፣ ለእኩልነት ፣ ለፍትህና ለአብሮነት መሆኑን ተናግሮ ለለውጡ ቀጣይነት የድርሻውን ለመወጣት ቃል ገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም