የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል አለበት-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ

79
ታህሳስ 27/2012 የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከያቤሎ እና ቡሌ ሆራ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ባካሄዱት ውይይት ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመሆን ነው ዛሬ ረፋዱ ላይ ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ የተገኙት። በቆይታቸውም ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። ነዋሪዎቹ በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በሰላምና ዴሞክራሲ መስክ ያከናወኑትን መልካም ተግባር አድንቀዋል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃይማኖት ተቋማት ተፈጥሮ የነበረውን ክፍፍል በመቅረፍ ረገድ ላበረከቱት አስተዋዕኦ ነዋሪው ምስጋና አቅርቧል። ነዋሪዎቹ አክለውም የመንገድ፣ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ አልሆንንም ሲሉም ቅሬታ አቅርበዋል። በተጨማሪም አካባቢው ካለው የቁም እንስሳ ሃብት አንጻር የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያ በአካባቢው ይገነባ ዘንድም ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰዓታት በኋላ ከያቤሎ ወደቡሌ ሆራ ከተማ በማቅናት ከነዋሪው ጋር ባካሄዱት ውይይት በተመሳሳይ የውሃና መንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው መንግስት በጀመረው የብልጽግና ጉዞ የዜጎችን ጥያቄ መፍታት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ነው ያሉት። በተያዘው ዓመት አገሪቱ በአጠቃላይ 50 ቢሊዮን ብር ለመንገድ መሰረተ ልማት በጀት መያዟን ጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥም 2 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በቡሌሆራና አካባቢው ለሚገነቡ መንገዶች የሚውል ነው ብለዋል። የክልሉ መንግስት ከሚመለከተው ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር ተቀናጅቶ የተነሳውን የውሃ ችግር ለመፍታት እንዲሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ሰጥተዋል። የአካበቢው ማህበረሰብ ብሎም የኦሮሞ ህዝብ ሌብነትን በመታገል እንዲሁም  አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ከኮንሶ -ያቤሎ- ዶሎ ኦዶ ድረስ የሚዘረጋ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ለመጀመር  የኮንትራት ሂደት መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል። በያቤሎ ከተማ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባትም የሚያስችል ሂደት መጠናቀቁን አክለዋል። የአካባቢው ህዝብ ለግጭት ከሚዳረጉት ጉዳዮች ራሱን ጠብቆ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በማሳሰብ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም