በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ ትምህርት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

61

 ኢዜአ ታህሳስ 27 /2012 በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ። የክልሉ ምክር ቤት አባላት በዩኒቨርሲቲው አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ መርሃ ግብር ለማስጀመር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከተቋሙ  ማህብረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክር ቤት አባል፣ የሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ  ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የአካባቢው ማህብረሰብ  በቅንጅት የጀመሩትን ሰራ እንዲያጠናክሩ ጠቁመዋል።

"በዩኒቨርሲቲው አሁን ላለው ሰላም የተማሪዎች ሚና ከፍተኛ ነው” ያሉት ወይዘሮ አለሚቱ ተማሪዎች ይህንኑ  መልካም  ተግባር ማስቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ለማሳካትና ቀጣይ ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ለትምህርታቸው ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ቀጣይ እንዲሆን ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል ።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ በዩኒቨርሲቲው አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ መርሃ ግብር ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረጉ ነው።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው  ከዩኒቨርሲቲውና ከአካባቢው ማህብረሰብ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታትና ተማሪውም የመጣበትን ዓላማ እንዲያሳካ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ መርሃ ግብር ለማስጀመር ከምክር ቤት አባላትና ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ያብባል ዘለቀ በሰጠው “በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩ የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካትና ነገን የተሻለ ህይወት እንዲኖረን ያግዛል” ብሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጸጥታ ችግር ባለመኖሩ የቤተሰቦች  ስጋት መቀነሱንም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም