በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ

107

ኢዜአ ታህሳስ 27/ 2012 በአማራ ክልል በግብርናው የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የተሻሻሉና ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ  ገለጸ። በግብርና ኢንቨስትመንት ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ የባለሃብቶች የምክክር መድረክ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በእዚህ ወቅት እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው ባለሃብት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።

ክልሉ ለግብርና ኢንቨስትመንት የተመቸና አዋጭ ዘርፍ ቢሆንም ባለሃብቱ ደፍሮ በመሰማራት በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ነው የገለጹት።

ደፍረው በመስኩ የተሰማሩት ባለሃብቶችም ቢሆን በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል የሚገጥማቸውን ችግሮች ተቋቁመው ወደ ሥራ በመግባት በኩል ውስንነቶች እንዳሉባቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ባለሃብቱ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ምርት በጥራትና በብዛት በማምረት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ማገዝ እንዳለበት አብራርተዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በገጠርና በከተማ ለሚገኘው ወጣት የሥራ ዕድል በመፍጠር ጠንካራ የመንግስት አጋዥ ሊሆኑ እንሚገባም ነው አቶ መላኩ ያመለከቱት።

የምክክር መድረኩ ዓላማም የግል ባለሃብቱ በዘርፉ የሚያቀርባቸውን ችግሮች ለይቶ በጋራ በመፍታት ለሥራእድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት ባለሃብቱ የሚፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሃብቱም በየደረጃው በሚገጥሙት ጥቃቅን ችግሮች ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት አሳስበዋል።

"በአማራ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንቨስትመንት ፍሰት" በሚል ጥናት ያቀረቡት የአማራ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ የጥናት ቡድን አስተባባሪ አቶ ሞገስ ተኬ በበኩላቸው በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የባለሃብቶች ፍሰት በሚጠበቅው ልክ አይደለም።

ባለፉት አስር ዓመታት በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍቃድ ከወሰዱት መካከል ወደሥራ የገቡት ስምንት በመቶ ብቻ መሆናቸውንም ለእዚህ በማሳያነት ገልፀዋል።

በዘርፉ ወደሥራ ይገባሉ ተብለው በተጠበቁት ባለሃብቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ከታሰበው ማሳካት የተቻለው 6 በመቶ ብቻ እንደሆነም አቶ መላኩ ተናግረዋል።

ለእዚህ ምክንያቱ መንግስት ለባለሃብቶች መስረተ ልማትን ከማሟላትና የብድር አቅርቦትን ከማመቻቸት አንጻር ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበትም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ባለሃብቶች ሁልጊዜ ያለቀለትና እንከን የለሽ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፈለግ ባለፈ ችግሮች ሲኖሩ ተጋፍጦ  ማሸነፍ አለመቻል የሚጠቀሱ ናቸው።

የዮኒና ዳኒ የእርሻ ልማት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ  መልካሙ አብረሃም በበኩላቸው በመንግስት  በኩል ከሚስተዋሉ ክፍተቶች መካከል የብድር  አቅርቦት ማመቻቸት ችግር የጎላው ነው።

ባለሃብቱም በሥራ ሂደት የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በራስ አቅም በመፍታት በኩል የሚስተዋልበት ክፍተት አለ።

በድርጅታቸው ለ50 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ የገለጹት አቶ መልካሙ፣ በርካታ ዜጎችን በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለሃብቱና መንግስት ተቀራርቦ መስረት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአባተ እና ማህሪ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ ማህሪ አዳነ  በበኩላቸው "መንግስት የግል ባለሃብቱን በአቅሙ ልክ እያገዘ አይደለም፤ ባለሃብቱም ምክንያት ፈላጊ ነው" ብለዋል።

በድርጅታቸው ለ100 ሠራተኞች የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ የግል ባለሃብቱ ችግሮችን ለመንግስት አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ በራሱ አሸንፎ ውጤታማ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ትናንት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም