የሴቶች ቱር ብስክሌት ውድድር በትራንስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

73
ኢዜአ ታህሳስ 26 ቀን 2012 ለአራት ቀናት በትግራይ ሲካሄድ የቆየው የሴቶች ቱር ብስክሌት ውድድር በትራንስ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ። "ቱር ብስክሌት ለአንድነት’’ የሚል ስያሜ በተሰጠው  የሴቶች ብስክሌት ውድድር መነሻውን መቐለ በማድረግ በዓብይ ዓዲ፣ በሃውዜን፣ ፍረወይኒ ውቅሮና መቀሌ  ከተሞችን ያካለለ  ነው። የብስክሌት ውድድሩ 347 ኪሎ ሜትር  የሸፈነ  መሆኑን የብስክሌት ውድድርና ስነ ስርአት አስተባባሪ መምህር ጸሐየ አደም ገልጸዋል። ውድድሩ የሜዳና የበረሃ ቦላታን ጨምሮ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት መሆኑን መምህር ፀሐየ አደም ገልጸዋል። በሜዳ ቮላታ ሰላም አማሃ ከትራንስ አንደኛ ስትወጣ ፤ ፀጋ ገብረ ከመስፍን እንዲሁም ትርሓስ ተክለሃይማኖት ከትራንስ አሸናፊዎች ሆነዋል። በዳገት ቮላታም ትርሓስ ተክለሃይማኖት፣ መርሃዊት ሓዱሽና ሰላም አማሃ ሦስቱም ከትራንስ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል። በውድድሩ ትራንስ፣ መሰቦ፣ መስፍንና 70 እንደርታ የብስክሌት ክለቦችን የወከሉ 24 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። በቱር ብስክሌት ውድድር ዛሬ 60 ኪሎ ሜትር በሸፈነና በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የከተማ ውድድር ላይ የትራንስ ተወዳዳሪዎች በአሸናፊነት አጠናቀዋል። በአጠቃላይ ውጤት ትርሓስ ተክለሃይማኖት፣ መርሃዊት ሓዱሽእና ምሕረት አስገዶም ሦስቱም ትራንስ ኢትዮጵያ የብስክሌት ክለብን የወከሉ ተወዳዳሪዎች አሸናፊዎች ሆነዋል። የትራንስ  የብስክሌት ክለብ በአጠቃላይ ውድድር አሸናፊ በመሆን የተዘጋጀለትን ዋንጫ የወሰደ ሲሆን የክለቡ አሰልጣኝ  መሓሪ ዱሪም ኮከብ አሰልጣኝ ተብሎ ሽልማት ወስዷል። ተወዳዳሪዎቹ ለውድድሩ የተዘጋጀውን ገንዘብና መዳሊያ ከትግራይ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ እጅ ተቀብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም