ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ የተሳተፈበት ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተካሄደ

98

ኢዜአ ፤ታህሳስ 26/2012 ከ200 ሺህ በላይ ስዎች የተሳተፉበት የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተካሄዷል።

ዜጎች ስፖርታዊ እንቀስቃሴዎችን ባህላቸው በማድረግ ለጤንነታቸው ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግን ያለመው ይህን ስፖርታዊ ሁነቱን በትብብር ያዘጋጁት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ  ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን ናቸው።

ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ በተካሄደው የማህበረስብ አቀፍ የጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴው ላይ ከ200 ሺህ በላይ የከተማው ነዋሪ  የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማንና ሌሎች ባለስልጣናት  ተሳትፈዋል።

ይህም ከዚህ በፊት በሩዋንዳ ተካሂዶ በነበረውና ከ120 ሺህ በላይ ህዝብ ከተሳተፈበት የሚበልጥ በመሆኑ ከአፍሪካ ክብረወሰን እንደሆነ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።

"ለአዲስ አበባ አረንጓዴነት እኔም የድርሻዬን እወጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከናወነው ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቀስቃሴ ላይ የስልጠና ፕሮጀክት ስፖርተኞች፣ ፌዴሬሽኖች፣ አንጋፋ አትሌቶችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች የዚህ ዝግጅት አድማቂዎች ነበሩ።

ይህን የማህበረሰብ የአካል ብቃት ስፖርት በሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋትና በዘርፉ ሰፊ ንቅናቄ መፍጠር ይቻል ዘንድ በየወሩ በተለያዩ ክልሎች በየተራ ለማከናወን መታቀዱም ተመልክቷል።

ቀጣዩን የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና አካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አዘጋጅ ለመለየት በወጣው እጣ መሰረት ባህርዳር በመጪው ወር አስተናጋጅ እንዲሆን ተመርጣለች።

በመቀጠልም ሐረሪ ፣ ሀዋሳ ፣ ጋምቤላ፣ ድሬድዋ ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ፣ መቀሌ እንደየቅደም ተከተላቸው የማህበረሰብ ስፖርት እንቀስቃሴን በየወሩ ያስተናግዳሉ።

ኦሮሚያ ክልልም ደግሞ የመጨረሻው የማህበረሰብ የጤናና አካል ብቃት ስፖርት አዘጋጅ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፣ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩርን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት በዚህ የማህበረሰብ ስፖርት ተካፋይ ሆነዋል።

በመርሃ ግብሩ እንካፈላለን ካሉ የተለያዩ ክለቦች፣ ፌደሬሽኖችና ሌሎች የስፖርቱ ቤተሰቦች የተሰበሰበ 100 ሺህ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ለሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች  ጉዳይ ሚኒስትር በእርዳታ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም