የፌዴራል ፖሊስ ከፖለቲካ ጫና ገለልተኛ ሆኖ የመስራት ጥረቱን ማጠናከር አለበት - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

157
ኢዜአ፤ ታህሳስ 24/2012 ፌዴራል ፖሊስ ከፖለቲካ ጫና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የመስክ ምልከታ ያደረገው የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የነበረውን የስራ እንቅስቃሴ ገምግሟል። ኮሚሽኑ ያደረጋቸውን ተቋማዊና አገራዊ የለውጥ ሂደቶች ለቋሚ ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ሰፊ ጥናት አካሂዶ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድቷል። ከዚህ አኳያ በህግ አሰራርና መዋቅር፣ በሰው ኃይል የመፈፀምና ማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ በሎጂስቲክስ አቅርቦት፣ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የነበሩ ክፍተቶችን በመፍታት ወደ ተግባር መግባቱንም አስታውቋል። ገለጻውን ያደመጠው ኮሚቴው በዘርፎቹ ላይ በማተኮር በተለይ የፀረ ኮንትሮባንድ ኃይል ራሱን ችሎ በዳይሬክቶሬት ደረጃ እንዲመራና በአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫዎች ፈጥኖ ደራሽ እንዲኖር መደረጉ ትልቅ ለውጥ በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብሏል። ህገ ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ከተለያዩ አገራት ጋር የነበረውን ስምምነት በማጠናከርና የመረጃ ልውውጡን በማጠናከር እየተደረገ ያለውን ጥረትም እንዲሁ። በተጨማሪም ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አጠበባበቅ አንጻር የምርመራ ሂደቶች በኃይል ሳይሆን የፖሊስ ሳይንስ በሚጠይቀው እውቀት ላይ እንዲመሰረቱና ግልፅነት እንዲኖር ከማድረግ አኳያም በተግባር የሚታዮ ለውጦች መኖራቸውን የቋሚ ኮሚው አባላት ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከአገር ውስጥ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ለመሳተፍ ግብረ ኃይል አሰልጥኖና የራሱን የዘመቻ ቁሳቁሶች አደራጅቶ ለማዝመት መዘጋጀቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። ከመከላከያ ሠራዊት የሠላም ማስከበር እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የፌዴራል ፖሊስ መጨመሩ ለገፅታ ግንባታና አገሪቷ ለሠላም ያላትን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ተናግረዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች፣ ከመከላከያና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር ያለው ትብብር እየተጠናከረ መሆኑንና የለውጥ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። አገራዊ ለውጡን ለማገዝም ይሁን ተቋማዊ ለውጡን ለመምራት ከህዝቡ ጋር መስራት ያስፈልገናል ያሉት ኮሚሽነሩ እየተፈጠረ ያለው ትስስር እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቷ የሚያጋጥሙ የወንጀል ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየሩ በመምጣታቸው ኮሚሽኑ በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዳለበትና ቋሚ ኮሚቴውም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ተሽከርካሪ፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ ድሮውን፣ ሄሊኮፕተርና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለኮሚሽኑ አስፈላጊ ተብለው ከተጠየቁ ቁሳቁሶች ዋናዎቹ ናቸው። ኮሚሽኑ በ2011 ዓ.ም የ123 ቢሊዮን 321 ሚሊዮን ብር የሙስና ምዝበራና የ15 ቢሊዮን የታክስ ማጭበርበር ወንጀሎችን የምርመራ ሂደቶች አጣርቶ ለህግ ማቅረቡን አስታውቋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም