የወጣቶችን ሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በማምረቻው ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ

56
(ኢዜአ) ታህሳስ 24 /2012 የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በማምረቻው ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት ቀዳሚ ሥራ መሆን እንዳለበት አንድ ጥናት አመለከተ። መቀለ ዩኒቨርሲቲ ከትግራይ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ ያስጠኑትን ጥናት በመቀሌ ከተማ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት ዶክተር ሺሻይ አማረ ናቸው። ዶክተር ሺሻይ በአንስተኛና መካከለኛ ማምረቻዎች ላይ የሚስተዋለውን የቦታና የፋይናንስ እጥረት አስመልክተው ባካሄዱት ጥናት ላይ እንደገለጹት፣ በዘርፉ የመንግስት ድጋፍ እጥረት፣ የፍትሃዊነትና የአጠቃቀም ጉድለት ችግሮች ይስተዋላሉ። በተጨማሪም የተደራሽነት፣ የመሰረተ ልማት ጉድለት፣ የቢሮክራሲና የገበያ ትስስር በአንስተኛና ማካከለኛ ማምረቻ ዘርፍ ከሚታዩ ማነቆዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ነው የገለጹት። ዶክተር ሺሻይ እንዳሉት መንግስት ለማምረቻ ተቋማት ያወጣውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለማድረጉ ዘርፍ የታሰበለትን ዓላማ እንዳያሳካ እንቅፋት ሆኗል። "ያልተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቂ የቦታና የማሽን ሊዝ አቅርቦት አለመኖር እንዲሁም ደካማ የሙስና ቁጥጥር ስርአት መኖር በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ሰዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረጉን ተናግረዋል። " በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ቅሬታ የሚያቀርቡበት ገለልተኛ ተቋም አለመኖርም ችግሩ በዘላቂነት እንዲቀጥል አድርጎታል" ብለዋል። ዘርፉ ድህነትን ለመቅረፍ ዋነኛ መሳሪያ ቢሆንም ዘርፉን ለመደገፍ የተቋቋሙ የመንግስት አካላት ድጋፍ ዝቅተኛ በመሆኑ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ መጓዝ እንዳልቻለ ዶክተር ሺሻይ አመላክቷል። "በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማምረቻው ዘርፍ የሚታዩ እነዚህን ማነቆዎች መፍታት ቀዳሚ ሥራ መሆን እንዳለበት በጥናቱ አመልክተዋል። ግልጽ የሆነ አሰራር መዘርጋት፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መቀመርና የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቅሬታ የሚያዳምጥና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ ገለልተኛ ተቋም አስፈላጊ መሆኑንም ነው በመፍትሄ ሀሳብ ያቀረቡት። "መንግስት በማምረቻው ዘርፉ ያወጣውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ባለመተግበሩ አብዛኞቹ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ለውጥ ማምጣት አልቻሉም" ያሉት ደግሞ በብረታ ብረት ማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ሙሉዓለም አለማየሁ ናቸው። መንግስት ለባለሀብቶች ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በማህበርና በግል ለተሰማሩ አነስተኛ የማምረቻ ዘርፍ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል። በዘርፉ አመራሮች የሚታይባቸው የተጠያቂነት ማነስና የስነምግባር ጉድለት ሌላው ማኖቆ መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ተናግረዋል። እንደእሳቸው ገለጻ በአመራሮች መካከል የተስተዋለው አለመናበብ ሌላው ዘርፉ እንዳያድግ ምክንያት ነው። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በበኩላቸው የማምረቻው ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ እድል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎች በጥናት እንዲመለሱ መደረጉ ለመንግስት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። "የማምረቻው ዘርፍ በሚፈለገው መጠን እያደገ አይደለም" ያሉት ዶክተር አብርሃም፣ በተለይ በፋይናንስና በማምረቻ ቦታ ትኩረት ተደርጎ ጥናት መደረጉ በዘርፉ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት አጋዥ ነው ብለዋል። "ዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጥናቱ የተለዩ የዘርፉ መነቆዎች እንዲፈቱ መስራት ይጠበቅባቸዋል" ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ ናቸው። በውይይት መድረኩ ላይ ከማምረቻ ተቋማት፣ ከተለያዩ የመንግስት ቢሮዎችና ከፋይናንስ ተቋማት የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝቷል። ጥናቱ መቀለ ዩኒቨርስቲና ከትግራይ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ ያካሄዱት መሆኑን ታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም