በትግራይ ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ድጋፍ ተጠየቀ

85
ኢዜአ ታህሳስ 24 / 2012 - በትግራይ ክልል ህገወጥ ስደትን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲያግዙ የክልሉ ምክት ቤት ጠየቀ። በክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተዘጋጀና ላለፉት ሁለት ቀናት በውቅሮ ከተማ በህገወጥ ስደት መከላከል ዙሪያ ሲመክር የቆየው  መድረክ ተጠናቋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ በወቅቱ እንደገለጹት የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን የተሰሚነት ሚና በመጠቀም ህገወጥ ስደትን ለመከላከል እየተደረ ያለውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል። "ህገወጥ ስደትን በተመለከተ በማህብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመለወጥ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትምህርት ሊሰጡ ይገባል" ብለዋል። ህብረተሰቡን በተሳሳተ ጎዳና እየመሩ ያሉ የህገወጥ ደላሎችና ሌሎች የወንጀሉ ተሳታፊዎችን ድርጊት በማውገዝ የመከላከሉን ስራ እንዲያግዙ አፈጉባኤው ጠይቀዋል ። የክልሉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ሓጎስ በበኩላቸው ህገወጥ ስደትን ለማስቀረት በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ተናግረዋል ። ስለ ድርጊቱ አስከፊነትና ጉዳት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተከናወነው ስራ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው አለመሆኑ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ካደረጉ ጉዳዩች አንዱ መሆኑን  ጠቅሰዋል ። "ወጣቶች በየበረሃው ሲቀሩና በህገወጥ ደላሎች ያልተገባ ክፍያ ሲጠየቁ ቤተሰቦቻቸው ለችግር የሚዳረጉባቸው አጋጣሚዎች እየሰፉና እየከፉ ናቸው" ብለዋል ። በህብረተሰቡ ውስጥ ስለጉዳዩ ያለውን የተዘባ አመለካከት ለመለወጥ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኃላፊዋ ጠይቀዋል። በምክክር መድረኩ ላይ "ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል የኃይማኖት መሪዎች ሚና" በሚል ርዕስ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በዩኒቨርሲቲው የስነ ህዝብ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ክንፈ አብርሃ በቀረበው ጥናት ባለፉት 15 ዓመታት አንድ ሚሊዮን 100ሺህ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በህገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት መሰደዳቸው ተመልክቷል። ከተሰደዱት ውስጥ 35 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በጥናቱ ተጠቅሷል። በጥናቱ መሰረት በህገወጥ ስደት በየበረሀው ሕይወታቸው ያለፈ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን በርካታ ቤተሰቦችም በችግር ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ህገወጥ ስደት ለድህነትና ስራ እጥነት መበራከት ዋንኛ ምክንያት መሆኑን የጠቀሰው ጥናቱ የተሻለ ስራ ፈለጋ የሚል የተሳሳተ አመለካከት ለስደት ዋንኛ መንሰኤ መሆኑን ተቁሟል። የህገወጥ ደላሎች የማታለያ ስልቶች ደግሞ ህብረተሰቡን ለተሳሳተ ግንዛቤ የሚዳርግና ለድርጊቱ መስፋፋት ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጥናቱ ጠቅሷል። ድርጊቱን ለመከላከል መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል የተቀናጀና ወጥነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ማካሄድ አንዱ  በመፍትሄነት ያስቀመጠው ጥናቱ ለተግባራዊነቱም የኃይማኖት መሪዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን አመላክቷል ። በክልሉ ምስራቃዊ ዞን አፅቢ ወንበርታ ወረዳ  የሀገር ሽማግሌ አቶ አታክልቲ እምባዬ በሰጡት አስተያየት ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ከቤተሰብ ጀምሮ ስለድርጊቱ አስከፊነት ማስተማር  እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። "ህብረተሰቡ ሁሌም ከኛ ጋር በመሆኑ ለመለወጥ ዝግጁ ነው" ያሉት ደግሞ በማይጨው ከተማ ነዋሪና የኃይማኖት አባት ሼህ ከድር ዓብዱልቃድር ናቸው። "በኃይማኖት መሪዎችና በአስተዳድር አካላት መካከል ያለውን ተቀናጅቶ የመስራት ክፍተት በመሙላት ድርጊቱን የመከላከል ስራን ውጤታማ ማድረግ ይገባል" ብለዋል ። ህገወጥ ስደትን ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት ኃላፊነታቸውን በበለጠ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል። በምክክር መድረኩ ከክልሉ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ከአንድ ሺህ በላይ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም