ለስታትስቲክስ አገልግሎት የማይውሉ የኩነቶች ምዝገባ በሥራ ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው

54
ኢዜአ ታህሳስ 23 / 2012 ዓ.ም በመደበኛነት ለስታትስቲክስ አገልግሎት የማይውሉ የኩነቶች ምዝገባ በስራችን ላይ ጫና ፈጥሯል ሲል የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታወቀ። በአስተዳደሩ የወሳኝ ኩነቶች መረጃ አቅርቦት ጥራትና ትንተና ቡድን መሪ አቶ ይስሀቅ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ወሳኝ ኩነት ለስታትሰቲክስ መረጃ  ከመጥቀሙ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ትክክልኛ መረጃ በመሰብሰብ የህዝቡን ቁጥር መሰረት ያደረጉ የልማት ሥራዎችን በዘላቂነት ለማከናወን አጋዥ መሆኑንም ገልፀዋል። ይሁንና ወቅት ያለፈባቸውና ለስታስቲክስ መረጃነት የማይውሉ ኩነቶች መደበኛ ስራውን ከማጉላላታቸው ባለፈ ህገ ወጥ ተግባራት እንዲስፋፉ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት በአራቱ ኩነቶች ውልድት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍች ኩነቶችን ከ25 ሺህ በላይ ለመመዝገብ ቢታቀደም ማከናወን የተቻለው ከ15 ሺህ በታች መሆኑን አመልክተዋል። ከመደበኛው ውጭ የሆኑና ለስታትስቲክስ ግብዓት የማይሆኑ ፖስፖርት፣ ንግድ ፍቃድና ሌሎች 16 ሺህ የሚጠጉ ምዝገባዎች በሥራው ላይ ጫና መፍጠራቸውን ገልጸዋል፣ "ከዚህ ውስጥ 13 ሺህ የሚሆነው ከኢሜግሬሽን ፓስፖርት ለማውጣት የኩነቶች መዝገባ ከሚካሄድባቸው ቀበሌዎች የልደት ካርድ የወሰዱ ናቸው" ብለዋል፡፡ ችግሩ ከአቅም በላይ እየተስፋፋ በመምጣቱ ባለፈው ወር ለ15 ቀን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀበሌዎች በተደረገ ፍተሻ 86 ግለሰቦች የሀሰት የልደት ካርድ አሰርተው መገኘታቸው መረጋገጡን ተናግረዋል። አቶ ይስሀቅ እንዳሉት በተለይ ታዳጊ ህጻናት 18 ዓመት ሳይሞላቸው እንደሞላቸው ተደርጎ የልደት ካርድ የሚሰራበት ሁኔታ ተስተውሏል። በተጨማሪም ያለ መኖሪያቸው ነዋሪ እንደሆኑ ተደርጎ የሚመዘገቡብትና በሌላ ክልል የሚኖሩ ግለሰቦችም ጭምር ተመዝግበው መገኘታቸውን አመልክተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠረጠሩ ሦስት የቀበሌ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን አቶ ይስሀቅ ገልጸው ከእዚህ ጋር በተያያዘ ደሴ ኢሚግሬሽን መታዋቂያና የልደት ካርዳቸውን ትተው የጠፉ በርካቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድም ከኢሜግሬሽንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች በዚህ በጀት ዓመት በአራቱም ኩነቶች ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን በወሳኝ ኩነት ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም