በፍንዳታ የተጎዱ ሰዎች በአብዛኛው ቀላልና በሕክምና የሚተርፉ ናቸው-የሕክምና ባለሙያዎች

65
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በድጋፍ ሰላማዊ ሰልፉ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአብዛኛው ቀላል የሚባልና በህክምና የሚተርፉ መሆናቸውን የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዕለቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨምሮ 86 ተጎጂዎችን አስተናግዷል። የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ በዕለቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 86 ያህሉ የሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል ማስተናገዱን ገልጸው፤ ጉዳታቸው በአብዛኛው "ቀላል መጫጫርና መጋጋጥ ነገር ነው" ብለዋል። በሆስፒታሉ የአጥንት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ በበኩላቸው ሆስፒታሉ አብዛኞቹ ጉዳተኞች "በአብዛኛው ቀላል የሚባልና ታክመው የሚተርፉ ናቸው" ብለዋል። በሆስፒታሉም ሁሉም የህክምና ክፍሎች ግብዓቶች አሟልተው እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ የተጎጅዎችን ሕይወት ለማትረፍ እየተረባረቡ መሆኑን ተናግረዋል። በአንድ ሰው ላይ በደረሰ ከፍተኛ ጉዳት የደም ቅዳ ቱቦ በመበጠሱ ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በመጨረሻ ሕይወቱን ማትረፍ አለማቸሉን ገልጸዋል። ዶክተር ወንድማገኝ "በኛ ሆስፒታል እስካሁን ባለን መረጃ 86 ሰዎች ታይተዋል። በሌሎች ሆሰፒታሎች የሄዱ ሰዎች አሉ። ከዚህ ውስጥም አምስቱ በከፍተኛ ሁኔታ ዋናው ቀዶ ህክምና ክፍል አሉ። ሶስት ደግሞ አጥንት ቀዶ ህክምና ክፍል አሉ። በአጠቃላይ ወደ ስምንት የሚሆኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አሉ። የአንድ ሰው ህይወት አልፏል እስካሁን ድረስ። አሁን ያለው አጠቃላይ መረጃ ይሄ ነው።” ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ “አጥንት ህክምና ክፍል ብዙዎቹ ቶሎ ቶሎ አክመናቸው የሚመለሱ ናቸው። ከነዚህም ሰዎች ከ13 በላይ ወደቤት እንዲሄዱ ተደርጓል። በዚህም አጋጣሚ ሁሉም አይነት ማህበረሰብ ነው የተጎዳው። ሐኪሞች ጭምር በዚህ አደጋ የተጠቁ አሉ። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ነው አደጋው የገጠመው። አብዛኛው እንደተገለጸው ቀለል ያሉና የሚተርፉ ናቸው።” የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው በመዲናዋ በሚገኙ ሆስፒታሎች ከ150 በላይ ተጎጅዎች ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ገልጸው፤ አብዛኞቹ መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና የአንድ ጉዳተኛ ሕይወት ከማለፉ በስተቀር ሌሎቹ አስፈላጊው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልጸው፤  ሆስፒታሎች በተገቢው ሁኔታ አገልግሎታቸውን አንዲሰጡና ህብረተሰቡም እንዲረጋጋ መልክት አስተላልዋል። ዶክተር ከበደ ወርቁ "ጉዳት የደረሰባቸወን በማረጋጋትና ህክምናቸውን አጠናክሮ መቀጠል ነው የሚጠበቀው። ለዚህም ሁሉም ሆስፒታሎች አመራሮቻቸው፤ ባለሙያዎቻቸው፣ እናንተው እየሄዳችሁ ያያችሁ ይመስለኛል። ከባድ አደጋ ነው የሚል እምነት የለንም።  ሰው እንዲረጋጋ ነው እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስተላለፍ የምፈልግው። ሌሎች ለውጦች ካሉ በቀጣይ እናሳውቃለን።" ከተጎዱ የሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል በምኒልክ ሆስፒታል ህክምና እያገኙ ያሉት ወጣት አብዱራህማንና ምኒልክ ሰማው ጥሩ የህክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል። አብድራህማን አህመድ  "የዶክተሮቹ እንክብካቤ በጣም ደስ ይላል፤ እንደ በፊት አይደለም ጥሩ እንክብካቤ ነው እያደረጉልን ያሉት”።      ምኒልክ ሰማው “በጣም በጣም እናመሰግናለን ዶክተሮቻችንን በጣም የተለየ አክብሮት መስጠት እፈልጋለሁ ምንም የጎደለብን ነገር የለም።”ብሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም