ፍንዳታውን አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

76
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በደረሰው ፍንዳታ እጃቸው አለበት የተባሉ ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፉ ላይ በመገኘት ለታዳሚዎች ከጥቂት ሰዓታት በፊት መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ፍንዳታ መድረሱ ይታወቃል። በፍንዳታው የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘይኑ ጀማል ለኢዜአ ገልጸዋል። ፍንዳታውን የሚያጠራ ጠንካራ የምርምራ ቡድን መቋቋሙንና ቡድኑ በተደራጀ ማስረጃ አስፈላጊውን ምርመራ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃዎችን እየተከታተለ ከስር ከስር ለህብረተሰቡ እእንደሚደርስ ጠቁመው፤ ከዚህ ውጪ ከተለያዩ አካላት በፍንዳታው ዙሪያ የሚነገሩ ሌሎች መረጃዎችን መቀበል እንደሌለበትም አሳስበዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 165 መድረሱንና ከነዚህም ውስጥ 15ቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ነው ኮሚሽነር ዘይኑ ያስረዱት። በመስቀል አደባባይ ለተደረገው ሰልፍ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በአዳባባዩ ቦታ መያዝ የጀመሩ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የሚያወድሱና አገራዊ አንድነትን የሚሰብኩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። መስቀል አደባባይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ሌሎች አመራር አባላት ፎቶ በታተመባቸው ቲ-ሸርቶች እንዲሁም በተለያዩ መልዕክቶች ባሸበረቁ ሰዎች ደምቆ ውሏል። የአደባባዩ ዙሪያዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት በተናገሯቸው የአንድነት መልዕክቶችና ጥቅሶች አሸብርቀው ነበር። ፍንዳታውን ተከትሎ በርካታ የፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው በማምራት የተፈጠረውን ክስተት አረጋግተው ህብረተሰቡ ወደየመጣበት እንዲመለስ ያደረጉ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም የድጋፍ ሰልፉን አጠናቆ ተመልሷል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም