የሙከራ የህዝብና የቤት ቆጠራ ሂደቱን ህብረተሰቡ መደገፍ እንዳለበት የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

76
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ላለው የሙከራ የህዝብና የቤት ቆጠራ ሂደት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ አገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ለአራተኛው ዙር የህዝብና የቤት ቆጠራ በአገሪቱ በሚገኙ 234 ጣቢያዎች ላይ የሙከራ ቆጠራ  እየተካሄደ ይገኛል። በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ኢዜአ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ ተገኝቶ ለመመልከት ችሏል። በከተማዋ የአዋሾ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋች በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ በአንድ የአስተዳደር ክልል ውስጥ ስላለው ህዝብ ብዛት፣ ስለ ህዝቡ ስነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህርያት ለማወቅ ይረዳል። ወቅታዊና አስተማማኝ የስነ-ህዝብና ማህበራዊ መረጃዎችን በማግኘት የህዝቡን የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። በመሆኑም በየአካባቢው ያለው የህብረተሰብ ክፍል የህዝብና የቤት ቆጠራው በሚካሄድበት ወቅት አስፈላጊውንና ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ በዳቱ ቡሌ ለህዝብና የቤት ቆጠራው የተዘጋጁ መጠይቆችንና ሌሎችንም ስራዎች በመከተል ህብረተሰቡ በአግባቡ ትብብር ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል። "የህዝብና የቤት ቆጠራን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በመረዳት ህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ምላሾችን መስጠት አለበት" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አስናቀች አጎናፍር ናቸው። ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ወይንሸት ተስፋዬ በበኩሏ “በማንኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህዝቦች ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ስራ  ለሚነሱ ጥያቄዎች በተገቢ ሁኔታ ምላሽ በመስጠት አገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል'' ብላለች። በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአራተኛው ዙር የህዝብና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን ጸሃፊ አቶ ሼኮ ጉሩ እንደገለጹት፤ እየተካሄደ ያለው የሙከራ ቆጠራ በዋናው ቆጠራ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በማጣራት ማሻሻያ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል። ስለሆነም የሙከራ ቆጠራው በሚደረግበት ወቅት ህብረተሰቡ ተገቢውንና አስፈላጊውን ትብብር ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። በአገሪቱ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተመረጡ አካባቢዎች የሙከራ ቆጠራ ከሚካሄድባቸው 234 ጣቢያዎች መካከል 161 የሚሆኑት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚደረግ ሲሆን 73ቱ ደግሞ በከተማ ላይ እየተካሄደ ይገኛል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም