በክልሉና በድሬዳዋ አስተዳደር በማህበረሰብ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

80
ኢዜአ ታህሳስ 22 /2012 በሐረሪ ክልልና በድሬዳዋ አስተዳደር በማህበረሰብ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮዽያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ገለጸ። በኤጀንሲው የሐረር፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ስራ አስኪያጅ አቶ ጉደታ አበበ ለአዜአ እንደገለጹት በድሬዳዋ አስተዳደርና በሐረሪ ክልል ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ቢጀመርም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ  አልተቻለም። ለዚህም በአካባቢው የሚከሰተው የጸጥታ ችግርና  አመራሩ ለስራው ያለው ቁርጠኝነት አነሳ መሆኑን እንደ ምክንያትነት ጠቅሰዋል። እስካሁን በተከናወነው ስራ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን 16 ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ከ188 ሺ በላይ አባ ወራና እማወራዎች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በመፈጸም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በክልሉና በአስተዳደሩ አገልግሎቱን ተግባራዊ ለማድረግ  ለአመራሩ እና ለሚዲያ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ አቅም የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በአምስት ወረዳዎች ላይ የሚጠበቅበትን 50 በመቶ አባላትን በምዝገባና ክፍያ ስርዓት እያሟላ በሚገኘው የሐረሪ ክልል “የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎትን” በቀጣይ ወራት ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። በድሬዳዋ አስተዳደር ግን ከሚፈለገው 36ሺ አባላት እስካሁን 3 በመቶ ላይ በመገኘቱ በዘንድሮ ዓመት ለማስጀመር አለማስቻሉን ተናግረዋል። በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት እንቅሰቃሴ በ2008 ዓ ም ቢጀመርም  ለማህበረሰቡ ግንዛቤን ከመፍጠር እና ከሌሎች ተግዳሮቶች ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉን የተናገሩት ደግሞ በሐረሪ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን መሀመድ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከናወነው የህዝቡ ንቅናቄን የመፍጠር  ስራ በክልሉ ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች መካከል አምስቱ የሚጠበቀውን ግዴታ በመወጣታቸው  ከጥር 10 ቀን 2012 ዓ ም አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ቢሮ የማህበረሰብ ጤና መድህን አስተባባሪ ሲስተር ሜሪ አምዴ በበኩላቸው በአስተዳደሩ በየጊዜው የሚከናወነው የአመራር  መለዋወጥ፣ የጸጥታ ችግርና ስራውን በባለቤትነት የሚያከናውን አለመኖር አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየታየ የሚገኘውን መረጋጋት በመጠቀምና ቢሮው ለስራው የለያቸውን ሰራተኞች በየቀበሌው በመመደብ እና ምዝገባ በማከናወን በዘንድሮ ዓመት በተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ አገልግሎቱን ለማስጀመር እንደሚሰራ ገልጸዋል። የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ጠቀሜታ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተግባራዊ ሆኖ ነዋሪዎች ሲጠቀሙበት በሚዲያ ተመልክቻለው የሚሉት የሐረር ከተማ ነዋሪ አቶ ከበደ ስሜ አገልግሎቱ በክልሉም  ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ''የጤና መድህን መንግስት ገንዘብ ሊሰበስብ ያቀደው እንጂ ለህብረተሰቡ ጤና አገልግሎት ሊሰጥበት አይደለም በሚል የተሳሳተ አመለካከት ይዘን ነበር'' የሚሉት በጉርሱም ወረዳ ሙየዲን ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሊያ ኡስማን ''ከወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ጋር ባደረግነው ውይይት ግንዛቤ አግኝተን 260 ብር በመክፈል አባል መሆንችያለው'' ብለዋል። በዚህም ''ልጄ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሐረር ከተማ በተላከበት ወቅት ለህክምና አገልግሎት ያወጣሁትን 17ሺ ብር የጤና መድህን አባል በመሆኔ በወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት አማካኝነት ገንዘቡ ሊመለስልኝ ችሏል'' ብለዋል፡፡ በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ክልል እንዲሁም  በአዲስ አበባ ከተ መስተዳድር በ509 ወረዳዎች የሚገኙ ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ጉደታ አበበ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም