አገር አቀፍ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ተከፈተ

120

ኢዜአ ታህሳስ 21/2012 ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ ሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተከፈተ። ኤግዚቢሽኑና ባዛሩ የተዘጋጀው "የተቀናጀ የገበያ ድጋፍ ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራት ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በተከፈተበት ስነ-ስርዓት ላይ የፌዴራል የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩማ ተወዳዳሪ የሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለአገራዊው ምጣኔ ኃብት ግንባታ የሚኖራቸውን ሚናን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአገራችን እየታየ ያለውን የስራ አጥነት ቁጥር በመቀነስና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ዓለው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመጠቆም።

በመክፈቻው ላይ የተገኙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂኒየር አይሻ መሐመድ እንዳሉት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተመርቀው ስራ እንዲፈጠርላቸው የሚጠብቁ ዜጋ ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ስራ ፈላጊ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ ዜጎች መሆናቸው ለሌሎች አርአያና ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህም በላይ በዘርፉ ተሰማርተው የተለያየ ችግር ያለባቸውም በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከችግራቸው ወጥተው የተሳካ ተግባር ይከውኑ ዘንድም አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡም ዘርፉን እንዲጠናከርና አገራዊ ፋይዳውም እንዲጎለብት የአገሩን ምርት በመግዛትና በመጠቀም ማበረታታት እንደሚገባም ሚኒስትሯ ያስገነዘቡት፡፡

የተቀናጀ የገበያ ድጋፍ ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራት ወሳኝ ነው በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር ከዛሬ ታህሳስ 21 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ለህዝብ ክፍት ይሆናል።

በአዲስ አበባ ጀሞ ቁጥር አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተከፈተው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 180 ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ የተመረጡት በተሰማሩባቸው መስኮች ጥራትን ጨምሮ ውጤታማ አፈፃፀም እያስመዘገቡ መሆናቸው የተረጋገጡ ናቸው።

በባዛሩ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የእንጨት ስራዎች እና ሌሎች በርካታ ምርቶች ለገበያ ቀርበዋል።

በኢንተርፕራይዞች መካከል የእርስ በእርስ የሥራ ትብብር ግንኙነት መፍጠር፣ የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማመቻቸት የባዛርና ኤግዚቢሽኑ ዓላማዎች ናቸው።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ሴት ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በአካል ጉዳተኞች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም