ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ

518

ታህሳስ 21 / 2012 ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እውን ይሆን ዘንድ የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በህዳሴው ግድብ ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ ስራዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አጠቃላይና ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ ኖሯቸው በአገራቸው ልማት ላይ ያለ ልዩነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስፈላጊው  በመሆኑ ነው።

በውይይቱም ግድቡ ገጥሞት ስለነበረው ችግርና አፈታቱ፣ በግድቡ ግንባታ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እያካሄዱት ስላለው ድርድር ሂደትና ቀጣይ እርምጃዎች ዙሪያ ለፖለቲ ካፓርቲዎቹ አመራር አባላት ገለፃ ተደርጓል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ በፖለቲካ ልዩነት ሳይገደቡ በአንድነት ልንሳተፍበት የሚገባ የአገር ልማት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በመሆኑም ግድቡ እውን ይሆን ዘንድ ህዝባዊ ተሳትፎው እንዲጠናከር ከማድረግ እስከ ገንዘብ መዋጮ ድረስ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ እንዲቀጥል፤ ወደፊትም እንዲህ አይነት ተግባር እንዳይፈፀም ጥንቃቄ እንዲደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራር አባላት አሳስበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የተወሰደውን እርምጃና የታየውን ለውጥ ተከትሎ ህዝቡ በአዲስ መልክ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ስላሴ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እስካሁን በውሃ ሙሌቱና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በርካታ ድርድሮች መካሄዳቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ድርድሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት አሳልፈን አንሰጥም ያሉት ኢንጂነሩ እስካሁን ድረስ በመካከላችን ምንም አይነት ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ አልገባም ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በግድቡ ግንባታ አጋጥመው የነበሩ ችግሮች ተፈተው ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ክረምት የውሃ ሙሌት በማካሄድ በሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ለመጀመር የሚቻልበት  የግንባታ ሥራው እየተፋጠነ ነው ብለዋል።