የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ ወሰነ

98

ኢዜአ፤ ታህሳስ 21/2012 የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ ውሳኔ አሳለፈ።

 የክልሉ  ካቢኔ በዛሬው እለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ እንዲጸድቁ ለጨፌ ኦሮሚያ መርቷል።

ካቢኔው ባካሄደው ስብሰባ ጥናትን መነሻ በማድረግ የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንደ አዲስ እንዲደራጅ ወስኗል።

የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው፤ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ለካቢኔው ባቀረበው ጥናት በዞኑ ባለው የመሰረተ ልማት እና የቦታ መራራቅ ችግር የተነሳ አገልግሎት በፍጥነት ማቅረብ ባለመቻሉ ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል።

ካቢኔው ጥናቱን መነሻ በማድረግ ውይይት ካካሄደ በኋላ የባሌ ዞን የነበረው፤ ምስራቅ ባሌ ዞን እና ምእራብ ባሌ ዞን ሆኖ እንደ አዲስ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ቢሮው አስታውቋል።

በውሳኔው መሠረትም የምእራብ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ እንዲሁም የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ጊኒር እንዲሆን የቀረበው ምክረ ሀሳብም በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ነው የተጠቆመው።

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ልማት አስተዳደርን ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እና የኦሮሚያ መንገዶች ፈንድን ለማቋቋም የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ለጨፌ ኦሮሚያ እንዲቀርብ ውሳኔ ማሳለፉን የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም