የወልድያ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 405 ተማሪዎችን አስመረቀ

63
ወልድያ ሰኔ 16/2010 የወልድያ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 405 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለአምስተኛ ጊዜ በ33 የትምህርት አይነቶች አሰልጥኖ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል ሁለት ሺህ 382ቱ  በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 23 ተማሪዎች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥኖ ያስመረቃቸው ሲሆን ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 922 ሴቶች መሆናቸው በምረቃው ስነስርዓት ተገልጿል፡፡ ለምሩቃኑ ዲግሪና ከፍተኛ ውጤት ላመጡት ደግሞ ልዩ ሽልማት የሰጡት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ወርቅሰሙ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት  መንግስት የዩኒቨርስቲዎችን ቁጥር ወደ 44 ያደረሰው ትምህርት የለውጥ መሳሪያ መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ ስለሆነም ምሩቃን እውቀታቸውን በሥራ በመተርጎም ሳይማር ያስተማራቸውን ህዝብ በቅንነት በማገልገል የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ በበኩላቸው እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው በሰለጠኑበት ሙያ ህዝብንና ሃገርን በታማኝነት በማገልገል ተደማሪ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው። ምሩቃኑ ባገኙት እውቀት ከጠባቂነት ተላቀው የራሳቸውን የስራ እድል በመፍጠር ጥሬ ሃብት እያላት በድህነት ውስጥ ለምትኖረው ሃገራቸው አለኝታነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት ለአገር ልማት የማይተካ ድርሻ አለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዩኒቨርስቲዎችን አቅም ለማጎልበት መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው የወልድያ ዩኒቨርስቲም በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በርካታ ህንፃዎችን ገንብቶ አቅሙን ማሳደጉን አስታውቀዋል። በጤና ሳይንስ ዘርፍ በአዋላጅ ሙያ የሰለጠነውና 3 ነጥብ 85 በማምጣት በማእርግ የተመረቀው ጌታሁን ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት በሰለጠነበት ሙያ ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል። በተለይም በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ህይዎት ለመታደግ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ተግቶ እንደሚሰራ አስታውቋል። በመሬት አስተዳደርና ቅየሳ ሙያ በ3 ነጥብ 97 በማምጣት በከፍተኛ ማእረግ የተመረቀው ማስረሻ ፈረደ በበኩሉ የሃገሪቱን የመሬት አያያዝና አስተዳደር ዘመናዊነትን እንዲላበስ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል። የወልድያ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብር የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር 20 ሺ170 መድረሱ ታውቋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም