ጥፋተኞችንና ተጎጅዎችንአገናኝተው እንደሚያስታርቁ ከአማራና ቅማንት የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ

61
በጎንደርና አካባቢው ተከሰቶ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥፋተኞችንና ተጎጅዎችን አገናኝተው እንደሚያስታርቁ ከአማራና ቅማንት ማህበረሰብ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡ እርቅ ለሰላም ግጭት ፈቺ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ማህበር ዛሬ በጎንደር ከተማ ጉዳት የደረሰባቸውን የሁለቱ ማህበረሰብ ክፍሎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአካባቢው አመራሮች ያሳተፈ ውይይት አካሂዷል። የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጀግናው ከበደ እንደተናገሩት የማህበሩ ዓላማ በግለሰቦችና በህዝቦች መካከል ያለን ጥል ማስቀረትና አንድነታቸውን በማጠናከር ሰላም የሰፈነበት አካባቢን መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመንግስት አካላትም ይሁን ለበጎ ዓላማ በተቋቋሙ የሀገር ሽማግሌ ቡድኖች በተደጋጋሚ የእርቅ ውይይት ቢደረግም አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንዳልተቻለ አውስተዋል፡፡ እንደ ማህበሩ ሰብሳቢ ገለጻ ዘላቂ ሰላም ያለመምጣቱ ምክንያት በዳይና ተበዳይ ሳይገናኙና ይቅር ሳይባባሉ በጉዳዩ ግንኙነት የሌላቸውን  በማወያየት የሚደረግ የእርቅ መድረክ በመሆኑ ነው። "ይህን መሰረታዊ ችግር የሀገር ሽማግሌዎች ማህበር በመገንዘቡ የበደለ ክሶ፣ ያላግባብ የወሰደ መልሶና የተበደለ ተክሶ ከልብ ይቅርታ የሚወርድበትን መንገድ ቀይሶ እየሰራ ይገኛል " ብለዋል። በዚህም ይቅር ተባብሎ በጋራና በመተባበር መንፈስ አንድነታቸውን ለመመለስ  እርቁን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን በማውረድ  የመፈጸም ስራ በቀጣይ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ከሁለቱ ህዝቦች የተመረጡ 388 አባላት ያሉት የሃገር ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ተመርጠው ወደ ስራ ለመግባት መሰማራታቸውን አስታውቀዋል። በየቀበሌው  የእርቁን ሂደት የሚያደናቅፉና ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርቡ የገለጸው ደግሞ የማህበሩ ፀሓፊ  አቶ አዳነ አዳምሰገድ ናቸው፡፡ "ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ በመካከላቸው ቂም ያለባቸውን ግለሰቦች እናስታርቃለን" ብለዋል። በወቅቱ በነበረው ግጭቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አቶ ደሴ አየነው በሰጡት አስተያየት "ይህ የእርቅ ስራ በሁለቱም ወገን በዳይና ተበዳይን የሚያገናኝ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደሚረዳ እምነት አለኝ "ብለዋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተወካይ  አቶ ሞላ መልካሙ  መንግስት የአካባቢውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ዓላማ ለተቋቋመው የሀገር ሽማግሌዎች ማህበር በመደገፍና የሚገጥማቸውን ችግር በጋራ በመፍታት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚደረግላቸውም አስታውቀዋል፡፡በጎንደር ከተማና አካባቢው ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲቆሙ የህዝቡን አንድነት መመለስና በጋራ ሰላማቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ እርቅ ለሰላም ግጭት ፈቺ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ማህበር በ2011 ዓ.ም. የተፈጠረውን ሁከትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደተቋቋመ ተመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም