ከሰኔ 15ቱ የባለስልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ ክስ የተመሰረተባቸው ያቀረቡት ክስ መቃወሚያ ውድቅ ሆነ

64

ኢዜአ ታህሳስ 21/2012 በሰኔ 15 በአዲስ አበባ እና ባሕርዳር ከተሞች ከተፈፀመው የባለስልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱት ግለሰቦች ያቀረቡትን መቃወሚያ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና  ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራን በመግደል የተጠረጠረው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡን ጨምሮ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ ሕዳር 12 ቀን 2012 ዓም ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ክሱ የተመሰረተባቸው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ አቶ አስጠራው ከበደ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣ አቶ አበበ ፈንታ፣ አቶ አስቻለው ወርቁ፣ አቶ ተሾመ መለሶ፣ አቶ ዓለምኔ ሙሌ፣ አቶ ከድር ሰኢድ፣ አቶ አየለ አስማረ፣ አቶ አማረ ካሴ፣ አቶ ፋንታሁን ሞላ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ በለጠ ካሳ ናቸው።

ተከሳሾቹ በዛሬው እለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ክሱን ያቀረበው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32 (1ሀ እና ለ)፣ 38 እና 238 (2) ድንጋጌን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን ገልጿል።

ተከሳሾቹም  ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓም ባቀረቡት መቃዋሚያ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ  ወንጀል ችሎት ዛሬ መልስ ሰጥቷል።

በዚህ መሰረትም ተከሳሾቹ ያቀረቡት ሁሉም የክስ መቃወሚያዎች ውድቅ የተደረጉ ሲሆን አቃቤ ሕግ አንዱን ክስ ብቻ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ተሰጥቶታል።

በዚህ የክስ መዝገብ የጄኔራል ሰዓረ መኮንንና  ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራን በመግደል የተጠረጠረው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ  "የቀረበብኝ ክስ ወንጀሉንና ሁኔታውን በዝርዝር የሚገልጽ አይደለም" በማለት መቃወሚያ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የቀረበው ክስ የወንጀሉን ሁኔታ በግልጽ ያስቀመጠ፣ ጊዜና ቦታውን ያሳየ፣ ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኝውም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በመሆኑ ወቃወሚያው ውድቅ መሆኑን አስረድቷል።

በዚሁ መዝገብ 3ኛ ተከሳሻ 'የጦር መሳሪያ ማስረከብ የለባችሁም በማለት ቅስቀሳ አድርገሐል' በሚል የቀረበብኝ ክስ ከእውነታው ጋር አይገናኝም የሚል መቃወሚያ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም መቃወሚያው ፍርድ ቤቱ ማስረጃ በሚሰማበት ወቅት የሚረጋገጥ መሆኑን በመጠቆም መቃወሚያውን ሳይቀበለው ቀርቷል።

በዚሁ የክስ መዝገብ ውስጥ 4ኛ፣ 5ኛ፣6ኛና 7ኛ በአቃቤ ሕግ የተከሰስንበት ወንጀል ተሳትፎን በተመለከተ  ለይቶ አላቀረበም ሲሉ የተቃወሙ ሲሆን ፍርድ ቤቱም መቃወሚያ በተመሳሳይ የክሱ ፍሬ ነገር ሲቀርብ የሚታይ በመሆኑ ውድቅ አድርጎታል።

በዚሁ የክስ መዝገብ 12ተኛ ላይ የተገለጹት አቶ ክርስቲያን ታደለ በሚያዚያ ወር 2011 ዓም በአማራ ክልል ባህርዳር፣ ደብረታቦር፣ጎንደር እና ወልደያ በመንቀሳቀስ ሰላምን የሚያውክ ቅስቀሳ የማድረግ ተልእኮ ተሰጥቶሃል ተብሎ የቀረበብኝ ክስ ትክክ አይደለም ቢልም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ ለአቃቤ ህግ ትእዛዝ የሰጠው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ 'በቀረበብኝ ክስ ላይ ጀነራሎቹ የተገደሉበት ቦታ ፣ለማምለጥ  የሞከርኩበት ቦታ እንዲሁም የተያዝኩበትን  አይገልጽም' በማለት ያቀረቡትን መቃወሚያ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤቶች ሕገ-መንግስታዊ መብቶቻችን እየተጣሱ ነው፣ ጠያቂዎቻችን እንዳይገቡ እየተደረገ ነው፣ ለምርመራ የተወሰዱ ንብረቶቻችን አልተመለሱም እንዲሁም እየተፈጸመብን ነው ያሏቸውን ሌሎች ችግሮች በመግለፅ አቤቱታ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱም ማረሚያ ቤቱ በቀረበው አቤቱታ ላይ መልስ እንዲሰጥ፤ አቃቤ ሕግም አሻሽል የተባለውን  ክስ ለመጠባበቅ ለጥር 8 ቀን 2012 ዓም ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም