የአፋር ክልል ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል...ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ

105
ታህሳስ 21 / 2012 በአፋር ክልል ከተሞች ለኑሮ ምቹና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ። በክልሉ በዓለም ባንክ ድጋፍ በከተማ አስተዳደሮች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለማጠናከር የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአመራሮችና ባለሙያዎች ተሰጥቷል። ለአምስት ቀናት የተሰጠው ስልጠና ሲጠናቀቅ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት  በክልሉ ስር የሚገኙ አብዛኛው ከተሞች  በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ባለፉት ዓመታት ለገጠር ልማት ያህል ለከተሞች እድገትና ልማት ትኩረት አለመሰጠቱን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ከተሞች ካላቸው የህዝብ ቁጥርና ከነዋሪዎች ስብጥር አንጻር በአግባቡ ከተሰራ የምጣኔ ሀብት እድገት ማዕከል ሊሆኑ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል ። በአንጻሩ ከተሞችን በአግባቡ መምራት ካልተቻለ የልማትና መልካም አስተዳደር እጦት ችግር ሊፈጥር የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩንም አመላክተዋል ። የክልሉ መንግስት በዘርፉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ  ለከተሞች የመሰረተ-ልማት መስፋፋት፣ ለአረንጓዴ ልማትና ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል ። "ከተማ አስተዳደሮች  የእድገት ፕላናቸውን መሰረት አድርገው በዝቅተኛ ወጪ እንዲለሙና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል"ብለዋል። የከተማ አስተዳደሮች ምከር ቤት ስለሌላቸው በራሳቸው የሚሰበስቡት ገቢ አለመኖርና በዓለም ባንክ ፕሮግራም አለመታቀፋቸው ለመልማት ትልቅ ችግር እንደነበረባቸው አስታውሰዋል ። አቶ አወል "ባለፈው  አንድ ዓመት ውስጥ ጊዜያዊ ምክር ቤት በማቋቋም ችግሩን መፍታት ተችሏል" ብለዋል። በበጀትና በተቋማዊ አቅም ግንባታ እንዲጠናከሩ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ለተግራዊነቱ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳደሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ። የአይሳኢታ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ አህመድ  በበኩላቸው ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የውስጥ ለውስጥ መንገድና የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የማዘመን ስራዎች ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። በልማት ስራዎቹም በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አመላክተዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከባንኩ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የውስጥ ለውስጥ መንገድግንባታና የዋና መንገድ ዳር የመብራት መስመር ዝርጋታ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሊ መሐመድ ናቸው። "ከተማዋ የእድገት ፕላኗን ጠብቃ ውብና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን መሰረት የጣሉ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል" እንደ ከንቲባው ገለጻ በጀት ዓመቱ ከዓለም ባንክ ፕሮግራም በተገኘ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተለያዩ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም