የህክምና ስህተቶችን አስመልከቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ

61
ኢዜአ ታህሳስ  31/2012 የህክምና ስህተቶችን አስመልከቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን የህክምና ባለሙያዎች ማህበር ያጠናው አንድ ጥናት አመለከተ። የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የህክምና ባለሙያዎች ስነ- ምግባርና የህክምና ስህተቶችን አስመልክቶ ከማህበሩ ጋር በመተባበር ዛሬ ለባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል። የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንዳሉት ባለፉት ጊዜያት በዓመት ቢበዛ ሁለት ያህል ብቻ ቅሬታ ይቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ጊዜ እስከ መቶ ቅሬታዎች በዓመት ከተገልጋዮች እንደሚቀርብ ጥናቱ አመልክቷል ብለዋል። ለዚህ እንደ ምክንያትነት ከጠቀሱት መካከል የህብረተሰቡ መብቱን የማስከበር ግንዛቤ ማድግ እንደሆነም ጠቁመዋል። ለቅሬታዎቹ መበራከትም የህክምና ባለሙያዎች የአቅም ማነስና ቸልተኝነት እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ ብለው ጋዜጠኞች ላቀረቡት ጥያቄ ለዚህ  ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልጋዋል ነው ያሉት። በጥናቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከታዩ 127 ቅሬታዎች 125ቱ ላይ ውሳኔ እንደተሰጣቸው አመልክተዋል። በዚህም 27 የሚሆኑት ቅሬታዎች የጤና ባለሙያዎችን ተጠያቂ ሲያደረግ 89 የሚሆኑት ግን በህክምና ባለሙያው የስነምግባር ጉድለት ያልታየባቸው መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። አብዛኛው ቅሬታ የቀረበው በማህጸንና የጽንስ ሃኪሞች ላይ ሲሆን ከ75 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በሆስፒታሎች ውስጥ የቀረበ ቅሬታ እንደሆነ ጠቁመዋል። ዘርፉ ሊመራበት የሚገባ ዘመናዊ የህግ ማዕቀፍና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስራም በስፋት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። በህክምና ላይ ለሚፈጠር የስነ ምግባር ችግር የሁሉንም አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅም ዶክተር ብርሃኑ አሳስበዋል። የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አታክልቲ ግደይ እንዳሉት ሰዎች  በህክምና የሚገባቸውን አገልግሎት በአግባቡ ሳያገኙ ሲቀሩ ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። አገልግሎት በመስጠቱ ሂደትም ባለሙያዎቹ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ እንዲሁ የሰው ህይወት ይጠፋል ነው ያሉት። ችግሩ ይህንን ያህል ክብደት ካለው አስቀድሞ ለመከላከል ስለ ሙስና ማወቅና መከላከል ያስፈልጋል ነው ያሉት ። በተጨማሪም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረትና ክተትል  ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሙስናን ለመከላከል ደግሞ ከራስ መጀመር በመሆኑ በጤና ተቋማት ላይ የሚፈጠረውን ችግር ለመፍታት ዛሬ የተዘገጀው መድረክ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም