የተከሰተው አሳዛኝ ክስተት መንግስት የጀመረውን የለውጥ ግስጋሴ ወደ ኋላ አይጎትተውም - የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

48
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 ዛሬ የተከሰተው አሳዛኝ ክስተት መንግስት የጀመረውን የለውጥ ግስጋሴ ወደ ኋላ እንደማይጎትተው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፉ ላይ በመገኘት ለታዳሚዎች ከጥቂት ሰዓታት በፊት መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ፍንዳታ መድረሱ ይታወቃል። ይህ አሳዛኝ ክስተት መንግስት ለጀመረው የለውጥ ግስጋሴ በቁጭት በማበርታት ተጨማሪ ጉልበት ይሆነው እንደሆን እንጂ በፍጹም ወደ ኋላ የሚጎትተው እንደማይሆን ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የአገራችን እና የህዝባችን ጠላቶች ሊገነዘቡት የሚገባው ትልቅ ቁምነገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሚመራው መንግስት እና በህዝባችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ማንም ሊያቆመው ያለመቻሉ ግልጽ እውነት ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ ። መንግስት የጉዳዩን ፈጻሚዎች ለህግ ለማቅረብ አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ ፖሊስ ምርመራውን እንዳጠናቀቀ ለህዝቡ እንደሚገለጽ ጽህፈት ቤቱ ጠቁሟል። የወንጀሉ ፈጻሚዎች ማንም ይሁኑ ማን ከክፋት ሀሳባቸው እና ከራሳቸው በስተቀር የሚወክሉት ምንም አካል እንደሌለ መንግስት በውል እንደሚረዳም ተመልክቷል። የአገራችን አድገት እና የህዝባችን አብሮነት ያልተዋጠላቸው ኃይሎች ባቀነባበሩት እኩይ ተግባር የተፈጸመው ድርጊት ግን እጅግ አሳዛኝ እና የከሰረ ተግባር ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው። ያለምንም የዘር፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎች ልዩነቶች የተካሄደው ይህ መድረክ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ውጤታማ የነበረ መሆኑንም አስታውቋል። የጥፋት ኃይሎቹ ሀሳብ እና ፍላጎት በምንም ዓይነት መልኩ ያልተሳካላቸው ከመሆኑም ባሻገር ይልቁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የለውጥ ጉዞውን ለማሰናከል ከሚፈልጉ አካላት በተጻራሪ በመቆም የማይናወጥ አንድነቱን በአደባባይ ማሳየቱ ተጠቅሷል። የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች የእኩይ ስራ ልክፍት ያለባቸው ጥቂት የከሰረ ፖለቲካ ጥማተኞች እንጂ ከማንም የሚደመሩ ሰዎች ባለመሆናቸው፣ ይህንኑ በመገንዘብ የአገራችን ህዝቦች በተለመደው የአርቆ አስተዋይነት መገለጫቸው አብሮነት እና መደመራቸውን እንዲያጸኑ መንግስት ጥሪውን ማቅረቡን መግለጫው አትቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል

ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ እና ለጓዶቻቸው የለውጥ ስራ በዛሬው እለት በተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈጠረው ችግር አስመልክቶ የተላከ መልእክት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በአንዳንድ የሀገራችን ከተሞች የተጠራው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገራችን እያሳዩ ላሉት ታላቅ የለውጥ ስራ ምስጋና እና ድጋፍ ለመስጠት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ የነበረው አጠቃላይ ድባብ እና የህዝባችን ጨዋነት የተሞላበት የማመስገን ስርዓት እጅግ ማራኪ እና ታሪካዊም ነበር፡፡ ሰልፉ የተጠራው በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት እና ቡድን ሳይሆን በሰፊው ህዝብ በመሆኑ እጅግ ስኬታማ እና ያማረ እንደነበር ከተስተዋለው ሁለንተናዊ ስኬታማ ፍሰት እና ኢትዮጵያዊ አብሮነት መረዳት ይቻላል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ያደረጉት ንግግር እና ያስተላለፉት መልእክት መላውን ህዝባችንን ያስደሰተ እና በፍቅር ያስተቃቀፈ እንደነበር እሙን ነው፡፡ ያለምንም የዘር፣ የሀይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎች ልዩነቶች የተካሄደው ይህ መድረክ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ውጤታማ የነበረ ሲሆን የሀገራችን አድገት እና የህዝባችን አብሮነት ያልተዋጠላቸው ሀይሎች ባቀነባበሩት እኩይ ተግባር የተፈጸመው ድርጊት ግን እጅግ አሳዛኝ እና የከሰረ ተግባር ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት መንግስት ለጀመረው የለውጥ ግስጋሴ በቁጭት ያበረታውና ተጨማሪ ጉልበት ይሆነው እንደሆን እንጂ በፍጹም ወደ ኋላ የሚጎትተው አይሆንም፡፡ የሀገራችን እና የህዝባችን ጠላቶች ሊገነዘቡት የሚገባው ትልቅ ቁምነገር በጠቅላይ ሚኒትር ዶክተር አብይ በሚመራው መንግስት እና በህዝባችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ማንም ሊያቆመው ያለመቻሉን ግልጽ እውነት ነው፡፡ በዛሬው የጥፋት አበጋዞች እኩይ ድርጊት ዜጎች ተጎድተው በህክምና እርዳታ ላይ የሚገኙ ሲሆን የጥቂቶቹ ጉዳት መጠንም ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል፡፡ መንግስት የጉዳዩን ፈጻሚዎች ለህግ ለማቅረብ አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ ፖሊስ ምርመራውን እንዳጠናቀቀ ለህዝባችን የምንገልጽ ይሆናል፡፡ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ማንም ይሁኑ ማን ከክፋት ሀሳባቸው እና ከራሳቸው በስተቀር የሚወክሉት ምንም አካል እንደሌለ መንግስት በውል ይረዳል። የጥፋት ሀይሎቹ ሀሳብ እና ፍላጎት በምንም ዓይነት መልኩ ያልተሳካላቸው ከመሆኑም ባሻገር ይልቁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የለውጥ ጉዞውን ለማሰናከል ከሚፈልጉ አካላት በተጻራሪ በመቆም የማይናወጥ አንድነቱን በአደባባይ አሳይቷል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ችግሩ በተፈጠረበት ቅጽበት ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹትም የመጠፋፋት አባዜ የተጸናወታቸው የሞት አበጋዞች ትላንትም አልተሳካላቸውም- ዛሬም አልተሳካላቸውም- ነገም አይሳካላቸውም፡፡ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች የእኩይ ስራ ልክፍት ያለባቸው ጥቂት የከሰረ ፖለቲካ ጥማተኞች እንጂ ከማንም የሚደመሩ ሰዎች ባለመሆናቸው ይህንኑ በመገንዘብ የሀገራችን ህዝቦች በተለመደው የአርቆ አስተዋይነት መገለጫቸው አብሮነት እና መደመራቸውን እንዲያጸኑ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም