የጅማ ሊሙ ገነት አስፓልት መንገድ ግንባታ የከተሞችን እድገት ለማፋጠንና ንግድን ለማነቃቃት ያግዛል- የሊሙ ኮሳ ነዋሪዎች

290

ኢዜአ ታህሳስ 18 ቀን 2012  ከጅማ ሊሙ ገነት ከተማ ያለው መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ ግንባታው መጀመሩ የአነስተኛ ከተሞች እድገትን ለማፋጠንና ንግድን ለማነቃቃት እንደሚያግዝ የሊሙ ኮሳ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የመንገዱን ግንባታ በይፋ አስጀምረዋል ።

የወረዳው ነዋሪዎች በስነ ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ የረዥም ጊዜ ጥያቄያቸውን የመለሰ ነው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ነዚፍ አባጀሃድ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አካባቢው ዋንኛ የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ቡና ጨምሮ ገበያ ተኮር  የግብርና ምርቶች የሚመረቱበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከአካባቢው የንግድ እንቅሰቃሴም ጋር ተያይዞ መንገዱ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት የሚያስተናግድ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይሁንና መንገዱ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ባለመሆኑ እንዲሁም ጠባብና ቶሎ ቶሎ ለብልሽት የሚጋለጥ መሆኑ ለትራንሰፖርት እንቅሰቃሴ አዳጋች ሆኖ ቆይታል" ብለዋል ።

መንገዱ ደረጃውን በጠበቀ አስፓልት መገንባቱ የትራንስፖርት ፍሰቱን ከማቀላጠፍ   በተጨማሪ በመስመሩ የሚገኙ የአነስተኛ ከተሞችን እድገት ለማፋጠንና የንግድ እንቅሰቃሴን ለማነቃቃት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

"የመንገዱ በአስፓልት ደረጃ መገንባት በአካባቢው የሚመረተውን ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቁም እንስሳትን በተሻለ ፍጥነት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አለሚቱ ከበደ ናቸው።

በአካባቢው በግብርና ምርት ማቀነባበር ለተሰማሩ ባለሃብቶችችም ምርታቸውን ተደራሽ ለማድረግና የተሻለ የገበያ አማራጭ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ አለሚቱ ገለጻ የመንገዱ መገንባት ጎብኝዎችና ባለሀብቶችን ለመሳብም አስተዋጻው የላቀ ነው ።

በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሊሙ ኮሳ ወረዳ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ትህጉን ቀሲስ መሰረት ወርቁ  መንገዱ ጠባብ፣ በተደጋጋሚ የሚበላሽና ለተሽከረካሪ አደጋ አጋላጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ መንገዱ ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰራ ቅሬታውን እስከ ፌደራል ድረስ  ለሚመለከታቸው አካላት ሲያቀርብ መቆየቱን አሰታውሰዋል ።

"የመንገዱ ግንባታ መጀመር ለጥያቄያችን ምላሽ እንድናገኝ አድርጎናል" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስለጣን ጀነራል ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ከጅማ ሊሙ ገነት ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ 92 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

መንገዱ ከ21 እስከ ስምንት ሜትር ስፋት እንዳለውም ጠቅሰዋል ።

በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ ሁለት ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ብር የሚገነባው መንገዱ በአራት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው የታቀደው።

እንደ ኢንጅነር ሀብታሙ ገለጻ መንገዱ የሚገነባው በቻይናው ቲ. ሲ. ጂ. ሲቪል ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም