ዘላቂ የልማት አጀንዳን ለማሳካት የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ማጎልበት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

102

ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 የዘላቂ የልማት አጀንዳን እውን ለማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚመክር ሃገር አቀፍ የምክከር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በመድረኩ  እንዳሉት የ2030 ዘላቂ የልማት አጀንዳን እውን እንዲሆን የአካል ጉዳተኞን ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ሚና ማጎልበት ይገባል።

ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ህብረተሰቡ ኃላፊነት ወስደው ካልሰሩ እቅዱን ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ከወትሮ በተለየ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንደ አገር ወደ ስኬት ከፍታ እንዲመጣ ዝርዝር እቅድ በማውጣት ለተግባራዊነቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዝርዝር እቅዱ ላይ ባለድርሻና አጋር አካላት የተሻለ ተነሳሽነት በማሳየታቸው መጪው ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች ብሩህ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ለአካል ጉዳተኞች መብትና ደህንንት መከበር እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ሁሉም አካል በትኩረት ሊረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው በሀገሪቱ ከሚገኘው 16 ሚሊዮን አካልጉዳተኞች ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ በድህነት ውሰጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ይህም በቅንጅትና ግንዛቤ ማነስ ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ከመሆኑም ሌላ አብዛኛው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዘላቂ የልማት ግቦች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ አካል ጉዳተኞችን ለመድረስ መንግሥት በትኩረት እንደሰራ አመልክተዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በዘንድሮ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ተሳታፊነታቸውን በማጎልበት ለዘላቂ የልማት ግብ መሳካት ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በተያዘው ዓመት የአካል ጉዳተኞችን ሁሉ አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሳሚራ ሱሉጣን ናቸው።

እያንዳንዱ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የእቅዳቸው አካል ማድረጋቸውን በማረጋገጥ የተሰራና ያልተሰራ ስራዎችን ለይተው ግብረ መልስ በመስጠት  የተሻለ እንዲሰራ ኮሚቴው ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አማካሪ አቶ መስፍን በረዳ በበኩላቸው" እንደ ሀገር በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተሰራው ስራ አዝጋሚ ቢሆንም ለውጦች ይታያሉ "ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች፣ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከሌሎችም የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም