ዛፍና ህይወት

86
ሰለሞን ተሰራ ኢዜአ በምስራቅ አፍሪካ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥና የደን መጨፍጨፍ የዝናብ አጥረት እየተከሰተ በመሆኑ የተራቆቱ ስፍራዎችን ለማዳንና ጥፋቱን ለመታደግ የችግሮቹን መንስኤ በመለየት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚገባ ሲነገር ቆይቷል። የዚህ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ ከሆኑት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች። የተፈጥሮ ደንን ለማገዶነት የመጠቀም ልማድ የአገሪቱን ደን በማራቆት በተደጋጋሚ ድርቅና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንድትጎዳ አድርጓታል። ይህንኑ ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ ዘመቻ ባለፈው ዓመት 2011 ዓም ሰኔ ወር  'አረንጓዴ አሻራ' በሚል መሪ ቃል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ በመትከል አንድ ብለው ጀምረውታል። “የአየር ጸባይ መለዋወጥ ኢትዮጵያን በጣም ጎድቷታል፤በዚህም ጎርፍ፣ድርቅና የምግብ ዋስትና አለመሟላት አጋጥሟታል” በማለት በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተጠሪ ማርጋሬት ኦዱክ ይናገራሉ። አክለውም “በአንድ በኩል በአገሪቱ ዝቅተኛ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ባጋጠማቸው የሙቀት መጨመርና ተደጋጋሚ ድርቅ እነሱና የህይወታቸው መሰረት የሆኑት የቀንድ ከብቶቻቸው ተጎድተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና ከባድ ጎርፍ እየተጠቁ የምርት እጥረት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል።” ይላሉ። ኢትዮጵያ 2009 ዓም ብቻ በድርቅ የተነሳ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ እንስሶችን በሞት ተነጥቃለች። ከዚህ ባለፈ የአካባቢ መራቆት፣ መሬትን ከሚገባው በላይ በመጠቀም የተነሳ ከፍተኛ የምርት እጥረት እየገጠማት ይገኛል የሚሉት ባለሙያዋ ዘላቂነት የሌለው የግብርና ልማድ፣ ልቅ ግጦሽና ለቤት ፍጆታ የሚውል ማገዶ ለቀማ የደን ሽፋኑን ከማመናመኑ ባለፈ የአፈር መሸርሸር እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ሲሉ በማከል። እናም ይህንን ፈተና በመጋፈጥ አገሪቱን መታደግ ይቻል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ባለፈው ዓመት ይፋ አድርገዋል። የአየር ጸባይ ለውጥንና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል ታስቦ በተነደፈው በዚህ መርሃ ግብር መሰረት በመላ አገሪቱ በ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 4 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ትልም ተቀይሷል። ይህም ለአንድ ሰው አርባ ችግኝ የመትከል ድርሻን ይሰጣል። ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅትም ተከላው ተግባራዊ ሆኗል። መንግስት የችግኝ ተከላ ዘመቻውን ለመከታተልና ውጤቱን ለመገምገም አምስት አባላትን የያዘ የኤክስፐርት ቡድን አዋቅሯል። አባላቱ ከአራት ተቋማት የተወጣጡ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና የአየር ጸባይ ለውጥ ኮሚሽን ይገኙበታል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር ሐምሌ 22 ቀን 2011 አከናውናለች። በዚህም ከተያዘው አቅድ በላይ  350 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል።  ብዙዎች እንደሚሉት ግን ዋናው ተግባር ይቀራል። ከፊት የሚጠብቅ ፈተና በችግኝ ተከላ ዋናው ፈተና የሚተከሉ ችግኞች ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የመጽደቃቸው እውነታ ነው። ብዙዎቹ ፈተናዎች ደግሞ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ ድርቅ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ይጠቀሳሉ። ለመቆጣጠር አዳጋች ከሆኑ ተጨማሪ እውነታዎች መካከል በእንስሳት መበላት አንዱ ነው፤ይህንኑ ለመከላከል ደግሞ አጥር መገንባት ወይም ጥሩ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ያስፈልጋል። “ኢትዮጵያ የችግኞች መጽደቅ ሚናው የጎላ መሆኑን በደንብ ተገንዝባለች።አገሪቱ ይህንኑ ግብ ለማሳካት የሚረዳትን አሉ የተባሉ ዘዴዎችን በመጠቀምና የአለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ በመጠየቅ ችግኞቹ እንዲጸድቁ እየሰራች ነው”በማለት ማርጋሬት ተናግረዋል። ክትትል አሁን ላይ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ጥረትን እየተከታተለ እንዳልሆነ ነገር ግን “ የተባበሩት መንግስታት ሊጀምረው ያሰበው የአስር አመት የአከባቢ ሁኔታ መልሶ ግንባታ ፕሮግራም (እኤአ ከ2021-2030) እውን ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ማህበር እና የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም በጋራ በመሆን በፕሮግራሙ የሚካተቱ አገሮችን የአከባቢ ሁኔታ መልሶ ግንባታ ተግባር የሚያግዙ ዳታዎችን እንሰበስባለን።” በማለት በመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም የከባቢ ሁኔታ ኤክስፐርት ቲም ክሪስቶፈርሰን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ “ቦን ቼንጅ “ በተባለ ማዕቀፍ በመታገዝ እኤአ እስከ 2030 ድረስ 15 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬቷን በደን ለመሸፈን አቅዳ እየሰራች ነው። “ይህን ያህል መጠን ያለው መሬት ደግሞ 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመያዝ ከበቂ በላይ ነው” ይላሉ ቲም ክሪስቶፈርሰን። “ ዛፍ መትከልና መሬትን ጎን ለጎን ለሌላ አገልግሎት ማዋል ጠቃሚ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፤ለምሳሌ ግብርናን አብሮ ማጣመር ይቻላል። ግብርናና የደን ልማት ፤ ችግኝ መትከልንና ግብርናን አጣምሮ የያዘ ሳይንስ ነው፤ይህም ከፍተኛ የምግብ ሰብል ምርትንና የመሬት ለምነትን ያሳድጋል።ለምሳሌ በዛፍ ተከልሎ የሚበቅለው ቡና ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።” በማለት ቲም ክሪስቶፈርሰን ጨምረው አስታወቀዋል። “ በአፍሪካ ከከባቢ አየር ናይትሮጅንን በመምጠጥ ለመሬት ማዳበሪያነት ለማዋል የሚችሉ በርካታ የዛፍ አይነቶች አሉ። በዚህም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ ይሰጣሉ። በርካታ ዛፍ መትከል የግብርና መሬትን ማጣበብ ነው የሚለው አመለካከት ፍጹም የተሳሳተ ነው። ቀጣይነት ያለው የግብርናና የደን ልማት በኢትዮጵያና በተቀሩት አገራት የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ብቸኛው መፍትሄ ነው” በማለት መናገራቸውን የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ድረ ገጽ ያሳያል። የተለያዩ ጥናታዊና ታሪካዊ ፅሁፎች ችግኝን በዘመቻ መትከል የተጀመረው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዘመን እንደሆነ ያስረዳሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት Status, Challenge and Opportunities of environmental Management in Ethiopia በሚል በታተመ ጆርናል ላይ በንጉስ ዘረዓ ያዕቆብ ዘመን በዘመቻ ከተተከሉና ተጠብቀው ከቆዩ ደኖች ወፍ ዋሻ፣ ጅባት፣ መናገሻ እና የየረር ተራሮች ጥብቅ ደኖች ተጠቅሰዋል። ከዚያም በኋላ አፄ ምንሊክ "ዘመናዊ" እፅዋትን ለኢትዮጵያ እንዳስተዋወቁ ይነገራል። በአገሪቱ ያለውን የማገዶና የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቀነስ የባህር ዛፍ ተክልን ከአውስትራሊያ እንዳስመጡ ይታወቃል። በወቅቱም የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል "ሁሉም በግለሰብ መሬት ላይ ያሉ ዛፎች የመንግሥት ንብረት ናቸው" ሲሉ አውጀው እንደነበር በዚሁ ጆርናል ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም