የእንስሳት አቅርቦት እጥረት የአገሪቱን የስጋ ወጪ ንግድ እያዳከመው ነው - የስጋ ላኪዎች

202

ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 በኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ለሚቀርብ የሥጋ ምርት የሚፈለገው እንስሳት ዝርያ በበቂ ሁኔታ አለመኖር የአገሪቱን የሥጋ ምርት ወጪ ንግድ እያዳከመው መሆኑን የስጋ ላኪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ኃብት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር በመሆኗ ለከብት እርባታና ሥጋ ምርት የተመቸች አገር መሆኗ ይነገራል።

በዚህም መሰረት በአገሪቱ በእንስሳት እርባታና ሥጋ ምርት በርካታ ኩባንያዎች ተመስርተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

እነዚህ ኩባንያዎች በተለይ የሥጋ ምርታቸውን በዋናነት የሚልኩት ወደመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንደሆነም ይነገራል።

በአጠቃላይ በእነዚህ አገራት በየዓመቱ አስር ሚሊዮን ያህል የፍየልና የበግ ሥጋ ይፈለጋል።

ሆኖም የኢትዮጵያ ላኪዎች በአቅርቦት ረገድ ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው በመሆኑ ይህንን ማስተናገድ እየቻሉ አለመሆኑን ይገልፃሉ።

በተለይ ዋናው ገበያ ለሚገኝበት መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚፈለገውን ሥጋ የሚሰጡት በጎችና ፍየሎች እጥረት በስራቸው ላይ እንቅፋት መሆኑን የኢትዮጵያ የስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ፀኃፊ አቶ አበባው መኮንን በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃል ተናግረዋል።

በአገራቱ የሚፈለገው የስጋ ምርት በአብዛኛው ከቆላማ አካባቢ በግና ፍየሎች የሚገኝ ስጋ መሆኑን ገልፀዋል።

የአካባቢው አገራት ዓመታዊ ፍላጎት አስር ሚሊዮን የቆላ በግና ፍየል ቢሆንም ላኪዎች ከገበያው ማግኘት የሚችሉት ከ2 ሚሊዬን አይበልጥም ብለዋል።

በአቅርቦቱ እጥረት ሳቢያም ላኪዎቹ ተፈላጊውን የእንስሳት አይነት በውድ ዋጋ ለመግዛት እንደሚገደዱ ተናግረዋል።

ይህም ላኪዎቹን በውጭ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ከማድረጉም በላይ የአገሪቱን የወጪ ንግድ እየጎዳው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ችግር ምክንያት ለኪሳራ ተዳርገው የተዘጉ ቄራዎች መኖራቸውን በማከል።

በእንስሳት አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በመቀነሱም ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ መቀነሱን አቶ አበባው ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ አምስት ወራት ወደውጭ ከተላከው የሥጋ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የ10 ሚሊዬን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን በመጥቀስ።

አቶ አበባው እንደገለጹት በአቅርቦቱ እጥረት ሳቢያ የስጋ አምራች ድርጅቶቹ የሚያመርቱት ምርት ከማምረት አቅማቸው 15 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው።

በባለድርሻ አካላት በኩል መፍትሄ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም ስራዎቹ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወኑ አይደለምም ይላሉ ዋና ፀኃፊው።

በዚህም ሳቢያ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሞጆ ዘመናዊ ኤክስፖርት ቄራ የንግድ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወይዘሮ አልማዝ አረጋ የግብይት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ደላሎች የእንስሳቱ ዋጋ እንዲጨምር አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ወይዘሮ አልማዝ እንደገለጹት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ባለሀብቶች የዘመናዊ እንስሳት እርባታ ላይ እንዲሰማሩ የተለያየ ኢንቨስትመንት ማበረታቻ መደረግ አለበት።

በአርብቶ አደሮችና በስጋ አምራችና ላኪዎች መካከል ቀጥታ የገበያ ትስስር መፍጠር፣  ለአርብቶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠትና ሌሎች መፍትሄዎችንም ወይዘሮ አልማዝ ጠቅሰዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የስጋ፣ ቆዳና ሌጦ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ አለሙ በበኩላቸው የስጋ ምርት ወደ ውጭ በሚልኩ ቄራዎች የሚፈለገው የቆላ እንስሳት አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

አሁን ባለው ባህላዊ የእንስሳት እርባታና ግብይት ሁኔታ ወደውጭ የሚላከውን ምርት ማሻሻልና የዘርፉን ችግሮች መፍታት ይቻላል ማለት የማይታሰብ ነው ሲሉም  አቶ ኢዮብ ይናገራሉ።

በመሆኑም የእንስሳት እርባታና ግብይቱን ወደ ዘመናዊ ስርዓት ማሸጋገር አስፈላጊ በመሆኑ ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን ባለኃብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አቶ ኢዮብ እንደገለጹት አርብቶ አደሮች አካባቢ ያሉ ወጣቶችን በማደራጀት ቀጥታ የግብይት ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባር ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው የእንስሳት ግብይት የሚከናወነው በህገ-ወጥ ንግድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህም የንግድ ልውውጥ ውስብስብ በመሆኑ ለመቆጣጠር የበርካታ ባለ ድርሻ አካላትን ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

የግብይት ስርዓቱን ማነቆዎች ለመፍታት የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ኮማንድ ፖስት በማደራጀት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም