በኢትዮጵያ የተጀመሩት ለውጦች ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ አይደናቀፍም-ኢህአዴግ

65
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ የተጀመረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ለውጥ  ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ ፈፅሞ ሊደናቀፍ እንደማይችል አረጋገጠ። ጽህፈት ቤቱ በዛሬው ዕለት በዶክተር አብይ አሕመድ መሪነት በአገሪቷ ለተጀመረው ለውጥ እውቅና ለመስጠት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በደረሰዉ ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን የገለጸ ሲሆን፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለመላ ኢትዮጵያዊያንም መጽናናትን ተመኝቷል ። ዶክተር አብይ አሕመድ በንግግራቸው ጥላቻና በቀልን ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን፤ ዘረኝነትንና ሙስናን ሳይሆን መደመርንና ሀገር ወዳድነትን በሰበኩበት የሚሊዮን ንፁህ ኢትዮጵያዊያን ታላቅ መድረክ ላይ የተፈፀመው ይህ የተሸናፊዎች የወንጀል ድርጊት ነው ብሏል መግለጫው። ድርጊቱ በመስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ ለአፍታም ሳይዘነጋ ተጠብቆ እንዲዘልቅ፤ የተጀመረው የፍቅር፣ የእርቅና የአንድነት ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚገፋ እንጂ ወደኋላ የሚጎትት አለመሆኑም ገልጿል። መላው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸውና በአደባባይ በመውጣት ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገራዊ አንድነት ያላቸውን ፅኑ እምነት እንዲሁም ለመሪያቸው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር የገለጹበትን መንገድ ጽህፈት ቤቱ አድንቋል። በቀጣይም የሕዝቡ ድጋፍ እንዲቀጥልና ትግሉ እንዲጠናከር  ጥሪውን አቅርቧል። ኢትዮጵያ ለፍቅር፣ ለይቅርታና አንድነት የዘረጋችው እጅ መቼም የማይታጠፍ መሆኑን በመረዳት ሕዘቡ በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛ ተግባሩን እንዲቀጥልም አሳስቧል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።  ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈ ቤት የተሰጠ መግለጫ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በዛሬው እለት “ለውጥን እንደግፍ፤ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በድርጅታችን ሊቀ መንበር ጓድ ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በሀገራችን ለተጀመረው ለውጥ እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ሀገራዊ አንድነታችንን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለማድነቅና ምስጋናን ለማቅረብ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በደረሰዉ ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል። የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለመላ ኢትዮጵያዊያንም መጽናናትን ይመኛል፡፡ ኢሕአዴግ ይህን የተስፋ መቁረጥና የጥላቻ ፖለቲካ መገለጫ የሆነ አፀያፊ ድርጊት በፅኑ እያወገዘ የተጀመረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ለውጥ ተስፋ የቆረጡ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ ፈፅሞ ሊደናቀፍ እንደማይችል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማረጋገጥ ይወዳል። የድርጅታችን ሊቀ መንበር ጓድ ዶክተር አብይ አህመድ በንግግራቸው ጥላቻና በቀልን ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን፤ ዘረኝነትንና ሙስናን ሳይሆን መደመርንና ሀገር ወዳድነትን ባከበሩበት የሚሊዮን ንፁህ ኢትዮጵያዊያን መድረክ ላይ የተፈፀመው ይህ የተሸናፊዎች የወንጀል ድርጊት በመስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ለአፍታም ሳንዘናጋ ጠብቀን እንድንዘልቅ፤ የጀመርነውን የፍቅር፣ የእርቅና የአንድነት ጉዞ አጠናክረን እንድንቀጥልበት የሚገፋን እንጂ ወደኋላ የሚጎትተን አይደለም። መላው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያችሁ አደባባይ በመውጣት ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገራዊ አንድነት ያላቸውን ፅኑ እምነት እንዲሁም ለመሪያችሁ ያላችሁን አክብሮትና ፍቅር የገለጻችሁበትን መንገድ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እያደነቀ ወደፊትም ከድርጅታችንና ከመሪያችን ጎን ቆማችሁ ትግላችሁን እንድታጠናክሩ ጥሪውን ያቀርባል። ኢትዮጵያ ለፍቅር፣ ለይቅርታና አንድነት የዘረጋችው እጅ መቼም የማይታጠፍ መሆኑን በመረዳት በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛ ተግባራችሁን እንድትቀጥሉም ከአደራ ጋር ያሳስባል። በአደጋው የሞቱትን ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት እንዲያኖርልን የቆሰሉትም በቶሎ እንዲያገግሙ እንመኛለን። ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን። የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሰኔ 16/2010 ዓ.ም              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም