ነገ በድሬዳዋ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል

71
ድሬዳዋ ሰኔ 16/2010 በድሬዳዋ ዋና ዋና አደባባዮችና ስታዲየም ነገ የሚካሄደው ታላቅ የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ያለውን የተቀናጀ ትብብር በማጠናከር ሰልፉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለመደገፍ ነገ በድሬዳዋ የሚካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በፖሊስ በኩል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፡፡ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፌደራል ፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አስፈላጊው ሥራ መሰራቱም ተመልክቷል። የድሬዳዋ ነዋሪ እንደወትሮው ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ያለውን የጠበቀ ትስስር በነገው ዕለት በሚካሄደው ሰልፍም በመድገም ህዝባዊ ሰልፉ ያለ ምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ኮሚሽኑ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል። በተለይ በነገው ሰልፍ ላይ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ይዞ ወደ ሰልፉ መግባት የተከለከለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስለታምና ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ መግባት የተከለከለ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡ በሰልፉ ላይ ህጻናትና አቅመ ደካሞች መገኘት እንደሌለባቸው ፖሊስ ኮሚሽኑ አሷስቧል። " እኛ ድሬዎች  ጥሪህን ሰምተን ተደምረናል" በሚል መሪ ሃሳብ  ነገ በሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ እስከ መቶ ሺህ ሰዎች ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሰልፉ አስተባባሪ ወጣቶች ትላንት ማስታወቃቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም