የብልጽግና ፓርቲ ከፋፋይ አሰራሮችን ካስወገደ የአገሪቱ ሰላም በአጭር ጊዜ እንደሚረጋገጥ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ገለጹ

66

ኢዜአ ታህሳስ 17 / 2012 የብልጽግና ፓርቲ ከፋፋይ አሰራሮችን በተግባር ከፈታ የአገሪቱ ሰላም በአጭር ጊዜ ይረጋገጣል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቨክ ማህበራት ተወካዮች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል የሆኑ ሶስት እህት ድርጅቶች እና አምስት አጋር ፓርቲዎች በመዋሃድ 'ብልጽግና' የተሰኘ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት  ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ አውቅ አግኝቷል ።

ቀድሞ የነበረው የፓርቲ አወቃቀር አንዱን ጠላት፣ ሌላውን ወዳጅ አድርጎ የሚፈርጅና ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔራዊ ማንነት ላይ ያተኮረ እንደነበር የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።

የኖዌጂያን ቸርች ኤድ የሰላም ፕሮግራም ሃላፊ አቶ መንግስቱ ጎንሳሞ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ታሪክ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል ላይ ያመዘነ በመሆኑ አብሮ የመኖር እሴትን ጎድቶታል።

''ቀድሞ የነበረው የፓርቲው አወቃቀር ዜጎች ልዩነታቸውን አክብረው በጋራ የመኖር ባህላቸውን ጎድቶት ቆይቷል'' ብለዋል።

''ውህዱ የብልጽግና ፓርቲ የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው'' ብለዋል።

ፓርቲው ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው ለአገራቸው ሰላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሊረዳቸው የሚችል እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።

ክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማህበር ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ወልደሰንበት በበኩላቸው በአብዛኛው የሚስተዋለው ክልላዊ አመለካከት የፌዴራል ሃይሉን አቅም አሳጥቶ አንድነትን እንደሸረሸረ ተናግረዋል።

ውህዱ ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን ክልላዊ አስተሳሰብ ወደ አገራዊ አንድነት በማሳደግ የዜጎችን ግጭትና መፈናቀል ይቀንሳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

''በአገሪቱ ግጭት ከቀነሰ ሁሉም ማህበራት በአገራዊ ልማት ላይ በማተኮር እድገትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሚና ይኖራቸዋል'' ብለዋል።

ብልጽግና  ፓርቲን የሚመሩ አመራሮች ተግባር ላይ መበርታት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

ከላይፍ ኤንድ ፒስ ኢንስቲትዩት የመጡት አቶ ፍሬው ከፍያለው በበኩላቸው ''የሲቨክ ማህበራት በአገሪቱ የተሰጣቸው በነጻነት የመደራጀት መብት በአግባቡ በመጠቀም ለአገራዊ አንድነት አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል።

ዜጎች መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲያውቁ በማድረግና መንግስትም አገር የማስተዳደር ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በመስራት ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

መንግስት የሲቨክ ማህበራት የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያድርጉ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ፍሬው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም